ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 20 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ የወጣቶች ንቅናቄ ተጀመረ

ሐረር፣ ሚያዝያ 16 / 2015 (ኢዜአ):-  የሐረሪ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ20 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ንቅናቄ ዛሬ አስጀምሯል።

በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ሸሪፍ ሙሜ በንቅናቄው የሊጉ አመራርና አባላት፣ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ አደረጃጀቶች እንደሚሳተፉ ገልጿል።

በክልሉ ዘጠኙ ወረዳዎች በተጀመረው ንቅናቄ 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግሯል።

ግድቡ አሁን የሚገኝበት ምዕራፍ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ በከፍተኛ መነቃቃት የሚያደርግበት ወቅት ነው ያለው ወጣት ሸሪፍ የግድቡ መጠናቀቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚፈታና የነገን ብሩህ ተስፋ የሚያሳይ ነው ብሏል።

የቦንድ ግዢው የወጣቶችን የቁጠባ ባህል ለማዳበር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑና በዚህ ረገድም ሁሉም ወጣቶች የቦንድ ግዢውን በመፈጸም አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርቧል።

የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አፈንዲ ሰለሞን ንቅናቄው የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶች በግድቡ ግንባታ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።  

በንቅናቄው ወጣቶቹ ቦንድ በመግዛት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች በበኩላቸው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢና የተለያዩ አማራጮች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በሐረሪ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከቦንድ ግዢና ከስጦታ ገቢ መሰብሰቡን ከክልሉ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም