ፍርድ ቤቱ በመስከረም አበራ ላይ ተጨማሪ 10 የምርመራ ቀናትን ፈቀደ - ኢዜአ አማርኛ
ፍርድ ቤቱ በመስከረም አበራ ላይ ተጨማሪ 10 የምርመራ ቀናትን ፈቀደ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2015 (ኢዜአ)፦ ፍርድ ቤቱ በመስከረም አበራ ላይ ተጨማሪ 10 የምርመራ ቀናትን ፈቀደ።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመስከረም አበራ አየለ ላይ ተጨማሪ 10 የምርመራ ቀናት የፈቀደ ሲሆን ሚያዚያ 26/2015 ዓ.ም የምትቀርብ ይሆናል።
ፖሊስ ተጠርጣሪዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፆቿ ማለትም በፌስቡክ ገጿና ኢትዮ ንቃት በተሰኘው የዩቲዩብ ቻናሏ በኩል ሁከትና ብጥብጥን አነሳስታለች ብሏል።
ይህም ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በኃይል ለመናድ የተቃጣ ድርጊት ነው ብሏል።
በአማራ ክልል የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀትን በተመለከተ በተሳሳተ መረጃ ጉዳዩ ወደ ሁከት እና ብጥብጥ እንዲቀየር በማድረጓ ነው በሚል አቅርቧል፡፡
በዚህም የሰዎች ህይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል ያለው ፖሊስ ባለፉት 13 ቀናት ለመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ ለመንግሥት እና የግል ባንኮች ደብዳቤ በመፃፍ ማስረጃዎችን የመሰብሰብ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አብራርቷል፡፡
በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ወደ ቦታው አቅንቶ ምርመራ ለማድረግ መቸገሩን በመግለፅ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡
ይህንን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ 10 ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ፈቀዶ ለሚያዚያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡