ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታን ይበልጥ ለማሻሻል የፖሊስ ኮሚሽነሮች ቅንጅታዊ ስራ መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 16/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እየተሻሻለ የመጣውን የፀጥታ ሁኔታ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የፌደራል፣ የክልልና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የፖሊስ ኮሚሽነሮች ቅንጅታዊ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።

14ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጉባኤው የኢትዮጵያ ፖሊስ በቀጣይ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደርስበት፣የተቀመጠው ራዕይ የሚሳካበትና የኢፌዴሪ ፖሊስ ዶክትሪን መሰረት ያደረጉ መስፈርቶች እንዲተገበሩ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን አስታውቀዋል።

እየተሻሻለ የመጣውን የፀጥታ ሁኔታ ይበልጥ ለማጠናከር ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አመልክተዋል።

የፖሊስ አገልግሎትን ለማሻሻልና የመፈጸም አቅምን ለማሳደግ በየደረጃው ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።


 

በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች የፖሊስን አገልግሎት በሚገባ አሻሽለው ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በ14ኛው የፖሊስ የኮሚሽነሮች ጉባኤ ላይ የፌደራል፣የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ኮሚሽነሮች የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም