ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች አገራት አርዓያ የሚሆን ነው - በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች አገራት አርዓያ የሚሆን ነው - በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች አገራት አርዓያ የሚሆን ነው ሲሉ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ተናገሩ።
አሜሪካ ለሰላም ስምምነቱ መጽናት በቀጣይ የሚጠበቅባትን ድጋፍ እንደምታደርግም ልዩ መልዕክተኛው አረጋግጠዋል፡፡
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት 'ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና' በሚል መሪ ሃሳብ የእውቅና እና ምስጋና መርሐግብር ትላንት በአዲስ አበባ ተከናውኗል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በፕሪቶሪያ የተደረሰው ሥምምነት አሜሪካ በአድናቆት ትመለከተዋለች ብለዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የተካሄደው ይኸው የሰላም ሥምምነት አሁን ላይ እዚህ በመድረሱ አሜሪካ የኢትዮጵያ አጋር አገር እንደመሆኗ ኩራት ይሰማታል ብለዋል።
ሥምምነቱ "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በማበጀት ረገድ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰላም ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቀጣይ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የጀመረችው የመልሶ ግንባታ ሥራ እና የሽግግር ፍትህን የማረጋገጥ ሂደትንም አሜሪካ ድጋፏን እንደምታጠናክር ተናግረዋል።
ይህንንም በተመለከተ ከመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ሁለት ዓመት የቆየችበትን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች አገራትም አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ጦርነት የዜጎችን ህይወት ከመቅጠፍ ውጭ ሌላ ዓላማ እንደሌለው በመገንዘብ ግጭቱን በማቆም ወደ ውይይት ሊመጡ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሜሪካም ከአፍሪካ ኅብረትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ከመሰሉ ተቋማት ጋር በመሆን ሱዳን ካጋጠማት ችግር እንድትወጣ ድጋፏን እንደምታደርግ ነው ያረጋገጡት።