ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እሴት ግንባታ አይነተኛ ሚና አላቸው - የሰላም ሚኒሰቴር 

ጅማ  ሚያዝያ 16/2015 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እሴት ግንባታ አይነተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት የሰላም ሚኒሰቴር ገለጸ።

የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እሴት ግንባታ ያላቸውን ሚና በተመለከተ የሰላም ሚኒስቴር ከሃይማኖት አባቶች ጋር ዛሬ በጅማ ከተማ መክሯል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒሰትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንዳአ እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እሴት ግንባታ ያላቸው አስተዋጽዎ ከፍተኛ ነው።

የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ሰባኪዎች እንደመሆናቸው በተለይም ሃይማኖትን የግጭት ምክንያት ለማድረግ የሚጥሩ እኩይ ሃይሎችን  በንቃት ሊከላከሉት ይገባል ብለዋል።


 

ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ግጭትና አለመግባባት እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል የወዳጅነትና የመቀራረብ እንዲሁም በአንድነት ለመኖር የሚያስችል እሴቶችን ማጎልበት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች የሰላም እሴትን ከመገንባት አንጻር የሚጫወቱት አዎንታዊ ሚና ተገንዝበው የሚከተላቸውን ምዕመን የማስተማርና የመምከር ሃላፊነት በትኩረት ሊወጡት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ተወካይ አቶ ታመነ ሳህሉ በበኩላቸው በሃይማኖት አባቶች የሚሰጥ አስተምህሮ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ይህ እሴት መቀጠል አለበት ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶችና አባገዳዎች ህብረተሰቡን በየእለቱ የማስተማር እድሉ ስላላቸው ሰላምን በመስበክና በማስረዳት የሰላም እሴቶቹን ለማጎልበት ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።

"የሃይማኖት አስምህሮ ለሰላም" በሚል ርእስ የውይይቱን መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡትና በሰላም ሚኒስቴር የአገር ግንባታ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አሰማ ረዲ እንዳሉት የሃይማኖት አባቶች የሰላም ግንባታ ሚናቸውን በትኩረት ለመተግበር  በቅድሚያ እርስ በርሳቸው ትብብርና ወንድማማችነትን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

በብዙ አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶች የሚነሱ ግጭቶችን ማስቆም እየቻሉ የመመልከት አዝማሚያ ይታያል ያሉት ወይዘሮ አሰማ፤ ይህ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በሃይማኖት ውስጥ የተደበቁ እኩይ ሃይሎችን የመመለስና እንዲሁም የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመገሰጽና በመምከር የማስቆም ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባኤ ጅማ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሃጂ ቢያ አባ መጫ እንዳሉት በጅማና አካባቢዋ ያሉ የሃይማኖት አባቶች በቅንጅት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በዚህም በአካባቢው የተሻለ ሰላም እንዲኖር ከማስቻላችንም በላይ ከተለያዩ ዞኖች ጋርም ልምድ በመለዋወጥ ሰላምና አብሮነትን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሃይማኖት ተቋማት የሰላም እሴት ግንባታ በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው የውይይት ላይ የፌደራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳዎች ተገኝተዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም