ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የጦርነትና የመከራ ጊዜ አብቅቶ፤ ትናንትን ተሻግረን ለነገ የተሻለ ለመስራት መዘጋጀት አለብን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 15/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የጦርነትና የመከራ ጊዜ አብቅቶ፤ ትናንትን ተሻግረን ለነገ የተሻለ ለመስራት መዘጋጀት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተከናውኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ በሰላም ሂደቱ ተሳትፎ ለነበራቸው አካላት ሁሉ እውቅና በመስጠት ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም ከጦርነት ወጥተን በሰላምና መልሶ ግንባታ ላይ እየተነጋገርን በመሆኑ የዛሬው እለት ለኢትዮጵያ ልዩ ቀን ነው ብለዋል።

ሰላም የተለየ ጊዜ አይፈልግም፣ የሰላም መቋጫ የምስጋናና የአዲስ ቀን ማብሰሪያ ናት በማለት እለቱ የመላ ኢትዮጵያውያን የደስታ ቀን መሆኑን ገልጸዋል።

ሰላም ጥላቻን ያፈርሳል፣ ጦርነት ደግሞ ጨለማ ነው፣ ያወድማል ይገድላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ጨለማ ወጥታ ወደ ሰላም ሂደቱ ፈቅዳ የጀመረችው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን ጠቅሰዋል፡፡

ከምክር ይልቅ መከራ የሚያስተምርን መሆን ስለሌለበት የጦርነትና የመከራ ጊዜ አብቅቶ፤ትናንትን ተሻግረን ለነገ የተሻለ ለመስራት መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

ከጦርነት ወጥተን በሰላምና መልሶ ግንባታ ላይ እየተነጋገርን በመሆኑ እለቱ የተለየ ቀን መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት መሪነት የሁሉም ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ወደ መቀሌ ይጓዛሉ ሲሉም ተናግረዋል።

ሰላማችንን በማቅናት በትብብርና አብሮነት ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ አኑረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም