ከሸኔ ጋር የሚደረገው የሰላም ንግግር ከነገ ወዲያ ይጀመራል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
ከሸኔ ጋር የሚደረገው የሰላም ንግግር ከነገ ወዲያ ይጀመራል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 15/2015"(ኢዜአ)፡- ከሸኔ ጋር የሚደረገው የሰላም ንግግር ከነገ ወዲያ በታንዛኒያ የሚጀመር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመርሐግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ እስካሁን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ብዙ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን በመጥቀስ ይህንን የሰላም ተግባር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ማስፋት ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በቅርቡ ከሸኔ ጋር በታንዛኒያ የሰላም ንግግር የሚጀመር መሆኑን ተናግረዋል።
ለሰላም ንግግሩ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የጦርነትና የመከራ ጊዜ አብቅቶ፤ ትናንትን ተሻግረን ለነገ የተሻለ ለመስራት ሁላችንም እንዘጋጅ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።