ቀጥታ፡

የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ከኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ተምረው በውይይት ወደ ሰላም አማራጭ ሊመጡ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 15/2015(ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ከኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ተምረው በውይይት ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ ጥሪ አቀረቡ።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ በአዲስ አበባ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ለጎረቤት አገራትና ለመላው አፍሪካውያን ትምህርት መሆኑን ተናግረዋል።

ሰላም ምክንያት አይፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርና ህዝብን ከሚያፈርስ ጥላቻ በመላቀቅ ፍቅርን ለሚገነባው ሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሱዳናውያንም ከኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ተምረው  ያጋጠማቸውን  ወቅታዊ ችግር በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ለሱዳን ወንድም ህዝብ ያላትን አጋርነት ለማሳየት ወደ ሱዳን በቅርቡ ሰብአዊ ድጋፍ ለመላክ መዘጋጀቷን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አገራት ሰላም አስከባሪ በመላክ ለሰላም ዘብ መቆሟን ጠቅሰው ፍቅርና አብሮነትን ለማጽናትም ካለን ላይ ቀንሰን ለሱዳናውያን ወገኖች አብሮነታችንን እናሳያለን፣ ሰላማቸውንም እንመኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም