በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት በጥሩ ምሳሌነት የሚወሰድ ነው- ሙሳ ፋኪ መሃማት - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት በጥሩ ምሳሌነት የሚወሰድ ነው- ሙሳ ፋኪ መሃማት
አዲስ አበባ ሚያዚያ 15/2015(ኢዜአ) ፡-በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት በጥሩ ምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ገለፁ።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም መንግስትና ህወሃት የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተገኘውን መልካም ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅና እና ምስጋና መርሐግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካ መፍትሄ በሚለው መርህ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ለተደረሰው ስምምነት ትልቅ ክብር ነው ብለዋል።
ሊቀመንበሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት የኢትዮጵያ ልምድ በአርዓያነቱ የሚወሰድ መሆኑን ገልፀው፤ የአፍሪካ ሕብረት በሰላም ሂደትና ግጭት አፈታት እምነት ተጥሎበት መምራቱም ትልቅ ክብርና ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነት ስኬት በሁሉም አካላት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለስምምነቱ መፈጸም ቀናዒ እና ቁርጠኛ ለሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት እና ለህወሃት አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የሌሎች ሀገራት መሪዎች፣ የድርድሩ መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አካላትም እንዲሁ።
የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍትሔ የማበጀት መርህ ተግባራዊ ማረጋገጫና ሌሎች አባል ሀገራትም ግጭቶች በአፍሪካ አቀፍ ሰላማዊ አማራጭ ወደ ስምምነት እንዲመጡ ህሊናዊ ሃላፊነት የሚጥል ነው ብለዋል።
የሰላም ሂደቱ በቀጣይ ፖለቲካዊ እና ሽግግር ፍትህ ሂደቶች ስኬታማ እንዲሆኑ በውሳኔውም መሰረት ሁሉም አካላት ለተፈጻሚነቱ በቅንነት ሊተባበሩ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም ፍላጎቱና ጥበቡ እንዳላቸው እምነታቸውን ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱ ቀጣይ ሂደቶችም ሴቶችን ጨምሮ አካታችነቱ የተጠበቀ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በጦርነቱ እና በሰላም ሂደቱ ባለፈችበት መንገድና ልምዷ በቀጣይ ለአፍሪካ ህብረት የመሪነት ሚና እንደሚኖራትም እምነታቸውን ተናግረዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ የሰላም ግንባታ እና ዘላቂ ልማት መረጋገጥ የህብረቱ ኮሚሽን የመደገፍ ሚናውን እንደሚወጣ አረጋግጠው፤ በዚህ ወቅት ሱዳን የገጠማትን ችግር ለመወጣት ከኢትዮጵያ ተሞከሮ ልትቀስም ይገባል ብለዋል።
አፍሪካ በግጭትና ጦርነቶች መልከ ብዙ ፈተናዎች እየተጋፈጠች መሆኑን ገልፀው፤ ሀገራዊ ግጭቶችን በሰላማዊ መፍትሄ በማረቅ አህጉራዊ ሰላምን ማረጋገጥ ሁሉም አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሀገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ደረጃ ትብብር ማጠናከር፣ ሰላምና መንፈሳዊ እሴት በመያዝ በልባችን ማተብ እና በአዕምሮ መሳል ይገባናልም ነው ያሉት።