በመንግስት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድሃኒት ቤቶች ዲጂታላይዝ የመድሃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመንግስት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድሃኒት ቤቶች ዲጂታላይዝ የመድሃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ ሚያዚያ 15/2015(ኢዜአ)፡-በመንግስት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድሃኒት ቤቶች ዲጂታላይዝ የመድሃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።
የመድሃኒት ግዢ ዲጂታል መደረጉ የመድሃኒት እጥረትን በማቃለልና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ፤ በተቋሙ የመድሃኒት አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማስፋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል ።
መድሃኒትን ከአገር ውስጥና ከተለያዩ የዓለም አገራት ገዝቶ በማከማቸት የማሰራጨትና ተደራሽ የማድረግ ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ቢሆንም በመድሃኒቶች መጋዘን ውስጥ እያሉ አልፎ አልፎ እጥረቶች የሚከሰቱበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የመድሃኒት ግዢ ዲጂታል መደረጉ የመድሃኒት እጥረትን በማቃለልና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የመድሃኒት ግዢና ስርጭት በማንዋል በነበረበት ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ እስከ 200 ቀናት ይፈጅ እንደነበር አስታውሰው ዲጂታል ከተደረገ በኋላ ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድሃኒት ቤቶችን በዲጂታል የመድሃኒት ግዢና ስርጭት መተግበሪያን ማስተሳሰር ተችሏል ነው ያሉት።
የመድሃኒት ክምችትና ስርጭትን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች የሚቀጥሉ መሆኑን ጠቅሰው አጋር አካላት የሚሳተፉበት ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጤና ተቋማት የመድሃኒት ክምችታቸውን በቀላሉ ለማወቅ የሚችሉበት የአሰራር ስርዓት እውን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በጤና ፕሮግራም የሚካተቱ መድሃኒቶችን ከክፍያ ነጻ በማድረግ ለተጠቃሚዎች በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችም ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በጤና ፕሮግራም የሚካተቱ መድሃኒቶችን በማቅረብ ከ95 በመቶ በላይ የተሳካ ስራ መከናወኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች 19 የመድሃኒት ማከማቻ መጋዘኖች መኖራቸውን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።