በኢትዮጵያ የምናከናውነውን የኢንቨስትመንት ሥራ ለማስፋፋት እየሰራን ነው - የሲሪላንካ ኩባንያዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የምናከናውነውን የኢንቨስትመንት ሥራ ለማስፋፋት እየሰራን ነው - የሲሪላንካ ኩባንያዎች
አዲስ አበባ ሚያዝያ 14/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ የሲሪላንካ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ሥራቸውን ለማስፋፋት እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ።
ኩባንያዎቹ ሌሎች የስሪላንካ ባለኃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ሥራ እንዲሰማሩ የማስተዋወቅ ሥራ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢንዶ ቻይን የልብስ አምራች ፋብሪካ የቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ አኖጅ ራናዌራ ኩባንያው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሥራውን ለማስፋት ፍላጎት አለው ብለዋል።
ከሰባት ዓመታት በፊት በአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራውን የጀመረው ኩባንያው አሁን ላይ ከ5 ሺህ በላይ ሰራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ኩባንያው ላለፉት ሦስት ዓመታት የጨርቃጨርቅ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ውጤታማ ሥራ በመሥራት ከኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚሰሩ ሠራተኞች ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት እንዳላቸው ጠቁመው ይህም ኩባንያቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።
የጃይ ጃይ የጨርቃጨርቅ ኩባንያ አስተዳዳሪ ዲላን ማዳሻንኩ ኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ያላት አገር መሆኗን ተናግረዋል።
በቦሌ ለሚ የሚገኘው ኩባንያው አሁን ላይ ለ10 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን አስታውቀዋል።
ኩባንያቸው ስኬታማ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የኢንቨስትመንት አማራጮች ሌሎች ባለኃብቶች መጥተው እንዲሳተፉም ጠቁመዋል።
የኬ ኤም ቢ ጨርቃጨርቅ ኩባንያ ዋና አስተዳዳሪ ባን ዳራ ዘርፉ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚፈልግ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ለዚህ ተመራጭ መሆኗን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉም የሲሪላንካ ኩባንያዎች ውጤታማ መሆናቸውንና ሌሎችም ባለኃብቶች ይህንን እድል ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አገሪቱ ያላትን የኢንቨስትመንት ኃብት ከግምት በማስገባት የሲሪላንካ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በግብርናና በኮንስትራክሽን ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ እያደረግን ነው ብለዋል።
አሪያ የተሰኘው የቅመማቅመምና ዘይት አስመጪና ላኪ ኩባንያ ዳይሬክተር ሮይ ሳማታናም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላይ የኢንቨስትመንት ሥራውን ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል።