ታላቁን የሕዳሴ ግድባችንን ለማጠናቀቅ አስተዋጽኦችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- በኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁን የሕዳሴ ግድባችንን ለማጠናቀቅ አስተዋጽኦችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- በኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች
መቱ ፤ ሚያዝያ 14 / 2015 (ኢዜአ)፡- እንደ ሀገር አንድ ሆነን የጀመርነውን የታላቁን የሕዳሴ ግድባችንን ለማጠናቀቅ የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በኢሉባቦር ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች አስታወቀ።
ዘንድሮ በዞኑ ለመሰብሰብ ካታቀደው ውስጥ እስካሁን ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል።
በኢሉባቦር ዞን በቦንድ ግዥ እየተሳተፉ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት፤ ግድቡ የአንድነት መገለጫ ከመሆኑም በላይ የእስካሁኑ ሂደት ግንባታውን ማሳካት እንደሚቻል ለዓለም ያረጋገጠ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ልማት ነው ።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ታመነ ወንድሙ፤ እስከአሁን በተለያዩ ጊዜያት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል የ100 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሀብት እንደመሆኑ እንደ ዜጋ የድርሻቸውን ለመወጣት አሻራውን ማሳረፋቸውንና እስከመጨረሻውም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
አቶ ስባቱ አረጋ በበኩላቸው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅምሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያሳብነውን ማሳካት እንደምንችል ለዓለም ያሳየነበት ፕሮጀክታችን ነው ብለዋል።
አንድ ሆነን በይቻላል መንፈስ የጀመርነውን ፕሮጀክታችንን አንድ ሆነን ለመጨረስና ያቀድነውን ማሳካት እንደምንችል ያረጋገጥንበት በመሆኑ ተሳትፏችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አስታውቀዋል።
የማንንም ድጋፍ ሳንጠይቅ በራሳችን አቅም እንችለዋለን ብለን የጀመርነውን ፕሮጀክታችንን አንድነታችንን አጠናክረን ማጠናቀቅ አለብን ያሉት ደግሞ አቶ ታረቀኝ ጉደታ ናቸው።
አስተያየት ሰጪዎቹ ግንባታው እየተገባደደ ለሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እስከመጨረሻው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኢሉባቦር ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋንታዬ አሰፋ እንዳመለከቱት፤ በዞኑ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው የኅብረተሰብ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ዘንድሮ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ እስካሁን ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ገንዘቡ የተሰበሰበው ከሁሉም ወረዳዎች በቦንድ ግዥ፣ በአጭር የፅሁፍ መልዕክትና በስጦታ መሆኑን ወይዘሮ ፋንታዬ አብራርተዋል።