በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 14/2015(ኢዜአ):- በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ያደርጋሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ42 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ፋሲል ከነማ በ27 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ሲገጥመው አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊግ መሪነቱን ለማጠናከር በአንጻሩ ፋሲል ከነማ ያለበትን ደረጃ ለማሻሻል የሚደረግ መሆኑ የጨዋታውን አጓጊነት ይበልጥ ይጨምረዋል።
በርካታ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎችም ለጨዋታው ደማቅ ድባብ ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሐ-ግብር ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ከነማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ተጠባቂውን ፍልሚያ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ-ግብር ድሬዳዋ ከተማና ሃዋሳ ከተማን ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ያገናኛል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሃዋሳ ከተማ በ31 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም።
ሶስት ጊዜ አሸንፏል ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ኢትዮ ኤሌትሪክን 2 ለ 0 እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።