ቀጥታ፡

አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን በሱዳን የተፈጠረውን ችግር የኢትዮጵያ ጣልቃገብነት እንዳለ አስመስለው የሚያናፈሱት መረጃ መሰረተ ቢስ ነው--የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2015(ኢዜአ)፦አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን በሱዳን ግጭት የኢትዮጵያ ጣልቃገብነት እንዳለ አስመስለው የሚያናፈሱት ሀሰተኛ እና መሰረተ ቢስ መረጃ ችግሩን አካባቢያዊ ለማድረግ ከሚመነጭ ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግስት በሱዳን የሚገኙ ዜጎቻችንን ሁኔታ እየተከታተለ መሆኑን ሚኒስቴሩ አረጋግጧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ወቅታዊውን የሱዳን ሁኔታ አስመልክቶ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በመንግስታት መለዋወጥ ያልዋዥቀ ጽኑ ወዳጅ ጎረቤት ሀገራት እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ሱዳን ካጋጠማት ወቅታዊ ፈተና እንድትወጣ ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታ ከሱዳናዊያን ጎን መሆኗን አረጋግጠዋል።

ያም ሆኖ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በግጭቱ የኢትዮጵያ ጣልቃገብነት እንዳለ አስመስለው የሚያናፈሱት መረጃ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት የማይመጥን መሰረተ ቢስና ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት በሱዳን የተፈጠረውን ችግር አካባቢያዊ ከማድረግ የመነጨ ፍላጎት መሆኑን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ መሪዎች ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ድረስ ሱዳን ያጋጠሟትን ችግሮች በሰላም እንድትፈታ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።

ዛሬም ሱዳን ያጋጠማት የሰላም መደፍረስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ የነበራትን ታሪካዊ ሚና ለመወጣት ሙሉ ፍላጎት እና ዝግጁነት እንዳላት አረጋግጠዋል።

ሱዳናዊያን ያለ ምንም የውጭ አካል ጣልቃ ገብነት ችግሮቻቸውን በራሳቸው ጥበብና ዕውቅት ይፈታሉ ብላ እንደምታምን ነው የተናገሩት።

ሚኒስቴሩ በሱዳን ወቅታዊ የፀጥታ መደፍረስን ተከትሎ በዋናው መስሪያ ቤት እና ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት በሀገሪቷ የሚገኙ ዜጎቻችንን ደህንነት ለማስጠበቅ በቅርበት እየተከታተለ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም የተለያዩ መስሪያ ቤቶችንና አጎራባች ክልሎችን በአባልነት ያቀፈ ግብረ-ኃይል በአገር አቀፍ ደረጃ መቋቋሙን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግጭት የገቡ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ተኩስ አቁመው ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም