የሀይማኖት ብዝሀነትን በማፅናት የአገርን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን -በድሬዳዋ የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የሀይማኖት ብዝሀነትን በማፅናት የአገርን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን -በድሬዳዋ የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች
ድሬዳዋ ሚያዝያ 13/2015 (ኢዜአ) የሀይማኖት ብዝሀነትን በማጽናት የአገርን ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በድሬዳዋ የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ገለጹ።
1ሺህ 444ኛው የኢድ አልፈጥር በአል ዛሬ በድሬዳዋ ተከብሯል ።
በከተማው የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች ዛሬ ከኢድ አል ፈጥር ስግደት መልስ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ያሰናዱትን "የእንኳን አደረሳችሁ" የቁርስ ዝግጅት አስተናግደዋል።
ዝግጅቱ የአንድነታችን መገለጫና ማሳያ ነው ሲሉ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ አገረ ስብከት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ መላከ ኃይል አባ ተስፋዬ አእምሮ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኅብረ ብሔራዊ የፍቅርና የአንድነት መገለጫዎችን በመጠበቅ ለአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት ይገባል።
"ቤተ ክርስቲያኗ ይህን ውበትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማፅናት የሀይማኖቱን ተከታዮች በማስተማር ኃላፊነቷን ለመወጣት ዝግጁ ናት" ብለዋል።
የደብረ ምህረት ቅዱስ ዑራኤል ዋና ፀሐፊ መላከ ወንጌል ቀሲስ ድርሻዬ በበኩላቸው "ዝግጅቱ የእርስ በርስ አንድነትና የድሬዳዋውን መገለጫ በማፅናት የተሻለ አገራዊና አካባቢያዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ያነቃቃል" ብለዋል።
"ወጣቶች ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በመጠበቅና በመንከባከብ የድሬዳዋ እንዲሁም የአገርን ዘላቂ ሰላም የመጠበቅ ድርሻችንን እንወጣለን "ያለው ደግሞ ዲያቆን ዮናስ አለማየሁ ነው።
"የድሬዳዋ ዓይነተኛ መገለጫ የሆነው አብሮነት የምንፈልጋትን አገር ለመንከባከብ መሠረታዊና ወሳኝ ነው ብሏል።
ወይዘሮ ኢንቲሳር ኢብራሂም በበኩላቸው "ይህን መሰል የእርስ በርስ መተባበርና ለአንድ አላማ በጋራ መቆም የድሬዳዋ ልዩ መገለጫ ነው" ብለዋል።
"ይህንን አንድነት መንከባከብና ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል" ሲሉም አክለዋል።
"ሰላም ለአገር ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ወሳኝ በመሆኑ ሰላማችንንና አንድነታችንን በተቀናጀ መንገድ በመጠበቅ የልማት ተጠቃሚ ለመሆን የድርሻችንን እንወጣለን" ያለው ደግሞ ወጣት ያሲን ሁሴን ነው።
በድሬዳዋ 1ሺህ 444ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የለውጥና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ አስታውቀዋል ።