ቀጥታ፡

የትግራይ ክልልን የንግድ እንቅስቃሴ የማነቃቃት አላማ ያለው የንግድ ባዛር በአራት የክልሉ ከተሞች ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ሚያዚያ 13/2015(ኢዜአ):- የትግራይ ክልልን የንግድ እንቅስቃሴ ማነቃቃት አላማ ያደረገ የንግድ ባዛር መቀሌን ጨምሮ በአራት የክልሉ ከተሞች ከሚያዚያ 21 ቀን 2015 ጀምሮ እንደሚካሄድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሰላም ትግራይ ተዘዋዋሪ ባዛር በሚል የተሰየመው ባዛር "የትግራይ የንግድ እንቅስቃሴ ለቀጠናዊ ሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከናወንና ለአንድ ወር እንደሚቆይ ተገልጿል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የትግራይ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግድ ባዛሩን አስመልክተው ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ባዛሩ ሚያዚያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመቀሌ ከተማ በይፋ እንደሚከፈትና በውቅሮ፣ አዲግራትና ማይጨው ከተሞችም እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

ከባዛሩ በተጨማሪ የፓናል ውይይት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

የንግድ ባዛሩን የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከአምነን ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ጋር እንዳዘጋጁት በመግለጫው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም