የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ
ድሬዳዋ ፤ ሚያዝያ 13/ 2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ዘላቂና ልማት መረጋገጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።
1 ሺህ 444ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬዳዋ በሰላት ስነ-ስርዓት በድምቀት ተከብሯል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ፤ የእምነቱ ተከታዮች የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማክበርና ልማቱ እንዲፋጠን እያበረከቱ የሚገኙትን ድጋፍና ትብብር አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አባልና የድሬደዋ ኡላማዎች ሰብሳቢ ሼህ አሚን ኢብሮ ፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጾም ወራትና ኢድ ሲያከናውነው የቆየውን የመደጋገፍ ፣ የመረዳዳትና የእርስ በእርስ አንድነት በዘላቂነት ማስቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
የአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው በዓሉን የእምነቱ አስተምህሮት በሚያዘው መሠረት በጾም ወራት የምናደርገውን መረዳዳትና መደጋገፍ በዘላቂነት ለመቀጠል እንተጋለን ብለዋል።
በሰላምና በልማት ጉዳዮች ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።