ቀጥታ፡

በአፍሪካ የቆዳ ውጤት ኢንዱስትሪን ለማስፋትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የንግድ ትርዒቶች ሚና የላቀ ነው--የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2015(ኢዜአ) በአፍሪካ የቆዳ ውጤት ኢንዱስትሪን ለማስፋትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የንግድ ትርዒቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።


 

13ኛው የመላው አፍሪካ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ትርዒት ''የሰው ልጆች መገኛ፤ የቆዳ መገኛ ናት'' በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።


 

አውደ-ርዕዩን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከቆዳ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም በኢትዮጵያ ከ500 በላይ ባለሀብቶች በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በአነስተኛ ደረጃ በዘርፉ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው 13ኛው የመላው አፍሪካ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የንግድ ትርዒት እንደ አገር ይዞት ከሚመጣው ዕድል ባሻገር በአህጉሪቷ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሬድማን በዳዳ በበኩላቸው፤ አውደ-ርዕዩ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያገናኝና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ነው።

በዚህም የንግድ አውደ-ርዕይ ዋና ዓላማም በዘርፉ ያሉትን ዕድሎች በመጠቀም በጋራ ለመሥራት ያስችላል ብለዋል።


 

በአውደ-ርዕዩ ላይ እየተሳተፉ ያሉ የቆዳ ውጤቶችን ይዘው የገቡ አምራቾች በበኩላቸው፤ የንግድ ትርዒቱ የአፍሪካን የእርስ በርስ የገበያ ትስስር ለማጠናከርና ልምድ ለመለዋወጥ ያግዛል ብለዋል።


 

በንግድና አውደ-ርዕዩ ላይ ከ200 በላይ የተለያዩ አገራት የቆዳ ውጤት አምራቾች፣ የማሽነሪዎችና ግብዓት አቅራቢዎች፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የገንዘብ ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ከሚያዝያ 12 እስከ 14/2015 በሚቆየው የንግድ ትርዒት ላይ 15ሺህ ሰዎች ይጎበሹታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም