ቀጥታ፡

በጌዴኦ ዞን ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ተጀመረ   

ዲላ፣ ሚያዝያ 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን "እኔም ድርሻ አለኝ" በሚል መሪ ቃል ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ መጀመሩን በብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ የዞኑ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በግድቡ ግንባታ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር "እኔም ድርሻ አለኝ" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ዛሬ በዲላ ከተማ ተጀምሯል።

ለአንድ ወር በሚቆየው መርሐ ግብር የቦንድ ሽያጭን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱም ተመላክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወጣት ስጦታ ገመዴ የቦንድ ሽያጭ ባስጀመረበት ወቅት እንደተናገረው፤ የዞኑ ወጣቶች ለግድቡ ግንባታ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሃሳብ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በዚህም ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጿል።

ከቦንድ ሽያጭ ባለፈ የተለያዩ የስፖርታዊና የኪነጥበብ ውድድሮች እንዲሁም በኩፖን ሽያጮች እቅዱን ለማሳካት እስከ ቀበሌ ድረስ የንቅናቄ መድረኮች እንደሚካሄዱም ሃላፊው ተናግሯል። 

ለዚህም የተጠናከረ የህዝብ ግንኙነትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በየደረጃው እየተካሄዱ መሆኑን የገለጸው ወጣት ስጦታ፣ የዞኑ ወጣቶች ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግ እንዲረባረቡ ጠይቋል።

የዞኑ ህዝብ እስካሁን የቦንድ ግዥ ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ለግድቡ ግንባታ መዋጣቱን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደሪቤ ጃኖ ናቸው።

በተያዘው ወር ወጣቶችን ጨምሮ ከኅብረተሰቡ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ግድቡ ለዛሬ ትውልድ ብቻ ሳይሆን፤ ለቀጣይ ትውልድ ታስቦ የሚሰራ የትውልድ ፕሮጀክት መሆኑን ያስረዱት ሃላፊው፣ ለዚህም የዞኑ ህዝብ ባለፉት ዓመታት ያሳየውን ተሳትፎ  እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

የአንድ ሺህ ብር ቦንድ ግዥ የፈጸመው ወጣት ኢዩኤል ተሾመ በሰጠው አስተያየትም ለግድቡ ግንባታ ቦንድ መግዛት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጿል።

ቦንዱ በግድቡ ግንባታ አሻራን ከማሳረፍ በተጨማሪ የቁጠባ ባህልን ለመልመድ እንደሚያስችል በመጠቆም።

''የእኛ አስተዋጽኦ እጅግ አስፈላጊ ነው'' ያለው ወጣት ኢዩኤል፣ ''ከእኛ የሚጠበቅብንን መስራትና የየራሳችን ድርሻ መውጣት አለብን'' ብሏል።

በመርሃ ግብሩ ወጣቶችና የወጣት አደረጃጀት ሃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም