ቀጥታ፡

ዩኒሴፍ 1 ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸውን የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶች ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2015(ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) 1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባቸውን የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶች ድጋፍ ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስረከበ።

ድጋፉን የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ዳውዳ ጊንዶ ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ አስረክበዋል።


 

ድጋፉ 60 የመድኃኒት ማጓጓዣ ጋሪዎች፣ አሥር የመድኃኒት ማውረጃና መጫኛ ማሽኖች፣ 8 ሺህ 186 የመድኃኒት መደርደሪያዎች ይገኙበታል።

በተጨማሪም 80 የቅዝቃዜ ሰንሰለት መከላከያ አልባሳት፣ አራት የክትትልና የቁጥጥር ካሜራዎችና አራት የአደጋ ጊዜ ጥሪ ማሳወቂያ ደውሎች በድጋፉ ተካተዋል።

የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ዳውዳ ጊንዶ፤ ኢትዮጵያ ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የምታከናውናቸው ተግባራት የሚበረታታ ነው።

ዩኒሴፍም አገሪቱ እያከናወነች ያለውን ጥረት በመደገፍ የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የግብዓት፣ የመድኃኒትና የክትባት ድጋፎችን በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በተፈጥሯዊና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ ዜጎች የሕክምናና መሰል ድጋፎችን እንዲያገኙ በማስቻል ረገድም እንዲሁ አጋርነቱን እየገለጸ ነው ብለዋል።

ዛሬ የተደረገው የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶች ድጋፍ ከ"ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን" በተገኘ 1 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ እገዛ የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።


 

በድጋፉ የቀረቡት ግብዓቶች ተቋሙ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት እንዲሰጥ የሚያስችሉና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በውስን የተቋሙ ማዕከላት አሁንም በሰው ኃይል መድኃኒቶችን የማጓጓዝ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸው ይህንን ለማስቀረት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት።

በዋናነት ዛሬ የተደረጉት ድጋፎች በጦርነቱ የወደሙና የግብዓት እጥረት ላለባቸው ማዕከላት የሚከፋፈሉ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም