በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወንድማማች ሕዝብ መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልእክት፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ በሚገኙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ የሐሰት ውንጀላዎችን በማሰራጨት የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ወገኖች እንዳሉ ጠቁመዋል።
እነዚህ ወገኖች በሃሰት ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሱዳን ድንበር አካባቢ አስገብታለች እያሉ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን መልካም ጉርብትና እና ግንኙነት ለማበላሸት ዓላማ ያላቸውን እነዚህን ውንጀላዎች አጥብቀን እናወግዛለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለው ወንድማማችነት እና መልካም ጉርብትና ዋጋ የምትሰጥ በመሆኗ የሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች የድንበር ጉዳይ በውይይት እና በውይይት ብቻ እንደሚፈታ በፅኑ እንደምታምንም ገልጸዋል።