ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን የማስፋትና አዳዲስ አሰራሮችን የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢትዮ-ቴሌኮም

አዲስ አበባ ሚያዚያ 12/2015?(ኢዜአ)፡-ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን የማስፋትና አዳዲስ አሰራሮችን የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።    

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ የጉምሩክ ቀረጥና የግብር ክፍያን በቴሌብር በቀላሉ መሰብሰብ የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራርመዋል። 

በዚህም ደንበኞች በተዘረጋው አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም በጉምሩክ ትሬድ ፖርታል  (www.customs.erca.gov.et) በመግባት አገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላቸውን ልዩ ልዩ መረጃዎችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

ደንበኞች የሚጠበቅባቸውን መረጃ አሟልተው ሲጨርሱ ኮሚሽኑ በሚሰጣቸው  የመክፈያ ቁጥር በቴሌብር ሱፐር አፕ ወይም በአጭር ቁጥር *127# ክፍያቸውን በአግባቡ የሚከፍሉበት ቴክኖሎጂ መሆኑን በመድረኩ ተጠቁሟል። 

ለሚከፍሉት ክፍያ ሕጋዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ደረሰኝ ከቴሌብር ሱፐር አፕ ላይ እንደሚያገኙም ነው የተገለፀው። 

ኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጎዳና ለማሳለጥ  ኃብት ና ጊዜ  በቆጠበ  መልኩ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። 

ይህንንም ለማድረግ ተቋማቶች የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ለዚህም ደግሞ ቴሌኮሙ አስፈላጊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋትና  አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። 

ቴሌኮሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ  የተቋማቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬውም ዕለት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር የተደረገው የሥምምነት ፊርማ የጉምሩክ ቀረጥና የግብር ክፍያን በቴሌብር ግልጽና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂውም አገሪቱ የጀመረቻቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴ ለማከናወን የሚያስችል ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ያግዛልም ነው ያሉት። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም