ቀጥታ፡

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከፈረንሳይ የኢኮኖሚ እና ባለብዙ ጉዳዮች ረዳት ጸሃፊ ዊልያም ሮስ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2015(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከፈረንሳይ የኢኮኖሚ ሚኒስቴር የባለብዙ ጉዳዮች ረዳት ጸሃፊ እና ከቡድን-20 ሀገራት የኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ተባባሪ ሰብሳቢ ዊሊያም ሮስ ጋር ተወያዩ።

ባለስልጣናቱ ውይይት የኢትዮጵያ የብድር ማገገሚያ ማዕቀፍ ጥያቄ በሚፋጠንበት እንዲሁም የአበዳሪዎች ኮሚቴ እያከናወነ በሚገኘው ተግባር ላይ የተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ውይይቱ በየካቲት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት የተፈራረሟቸው የትብብር ስምምነቶች የደረሱበትን ደረጃ ለመገምገም ዕድል መስጠቱም ተገልጿል።

በተጨማሪም የፈረንሳይ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በመሰረተ-ልማት፣ በኮሙኒኬሽን፣ በትራንስፖርት፣ በግብርናና ሌሎች የሁለትዮሽ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንቶች ላይ ውይይት ተደርጓል።

ኢትዮጵያ የብድር ማገገሚያ ማዕቀፍ ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ የፈረንሳይና የቻይና መንግስታት የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ማቋቋማቸው የሚታወስ ነው።

ኮሚቴው በኢትዮጵያ የብድር ማገገሚያ ጥያቄ እንዲሁም ለሀገሪቱ አስፈላጊ የፋይናንስ ዋስትና መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለአምስት ግዜያት መወያየቱም ተጠቁሟል።

ኮሚቴው አሁን ያለበትን ሁኔታ ለሚኒስትሩ ማብራራታቸውና የኮሚቴው አባል ሀገራት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ፕሮግራሞች ትይዩ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዋስትና ለመስጠት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ዊሊያም ሮስ አስታውቀዋል።

የብድር ኮሚቴው የኢትዮጵያን የብድር ማገገሚያ ጥያቄ በፍጥነት ለመመልከት ያለውን ቁርጠኝነት ጨምረው ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው በርካታ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውጤታማ የኢንቨስትመንት ስራዎቸ እያከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የፈረንሳይ ባለሀብቶች መዋዕለ-ነዋያቸውን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱ ለማበረታታት ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር እንደሚሰሩ አቶ አህመድ ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ባለሀብቶች በቅርቡ ለግሉ ዘርፍ ክፍት የተደረጉ ዘርፎች ላይ መዋዕ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀው ቀጣይነት ያላቸው የኢንቨስትመንት ውይይቶችን ለማድረግ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም