ቀጥታ፡

በረመዳን የፆም ወቅት የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና በማገዝ የታየው መልካም ተግባር በቀጣይም መጠናከር አለበት -የእምነቱ ተከታዮች

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2015(ኢዜአ)፦በረመዳን የፆም ወቅት የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና በማገዝ የታየው መልካም ተግባር  በቀጣይም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት የእምነቱ ተከታዮች ተናገሩ።  

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኸ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ የዒድ አልፈጥር በዓል ጨረቃ ዛሬ ማታ ከታየች ዓርብ፤ ካልታየች ደግሞ ቅዳሜ ተከብሮ የሚውል መሆኑን አስታውቀዋል። 

ከበዓሉ አከባበር ጋር ኢዜአ በአዲስ አበባ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች ዒድ ሲከበር በአብሮነት፣ በመስጠትና በመተዛዘን ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

በረመዳን ፆም ከቂምና ጥላቻ በመራቅ በመልካም ነገሮች ላይ በማተኮር፤ በስግደትና ብርቱ ፀሎት/ዱአ/ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም መቀጠል አለበት ብለዋል።

የዒድ በዓልን ስናከብር ሁላችንም ካለን ላይ ቀንሰን ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል መሆን አለበትም ነው ያሉት።

ለችግረኞች የሚሰጠው በእምነቱ  ተከታዮች “ዘካተል ፊጥር” በመባል የሚታወቀው የመስጠት ሂደት በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ ሊከናወን ይገባል ነው ያሉት።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሸመከተ ሙሄ፤ በዒድ አልፈጥር የተቸገሩትን ለማገዝ እንዲሁም ከሌሎች እምነት ተከታዮችም ጋር በደስታ ለማክበር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መሃመድ አሚን አደም በበኩሉ፤ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በበዓሉ ወቅት በመተጋገዝና በመደጋገፍ ኃይማኖታዊ ኃላፊነትን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል። 


 

አስተያየት ሰጪዎቹ እነዚህንም በጎ ተግባራት ከዒድ አልፈጥር በኋላም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ ሌላውም ሙስሊም ማኅበረሰብ በጎ አድራጎቱን ማስቀጠል አለበት ነው ያሉት። 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አዚዛ ሙሳ በረመዳን ወቅት ሲደረጉ የቆዩ መልካም ተግባራት ከረመዳን በኃላም አስፈላጊና ሊዘወተሩ እንደሚገባ ገልጻለች።

በሌላው ጊዜ የሚደረግ በጎ ተግባርም እንደ ረመዳን ወራት በረከት የሚገኝባቸው መሆኑን በመጠቆም።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ሳሊሀት ሙህዲን በበኩሏ፤ በቤትና በአካባቢ ላይ የተጀመሩ በጎ ተግባር ለትልቅ ደረጃ እንደሚበቃ ገልጻለች።

ይህ ትንሽ ጅማሬ ነገ ላይ እየሰፋ ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ተናግራለች።

በረመዳን ወቅት የነበረው አቅመ ደካሞችን የመርዳትና ሌሎችም በልተው እንዲያድሩ የማድረግ ተግባር የዕለት ተለት ሥራ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝባለች።


 

መረዳዳት አንድ የህይወት መርህ ሊሆን ይገባል ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መካነሰላም መሃመድ ነች።

የረመዳን ወቅት መልካም ሥራዎች የሚበዙበት መሆኑን ገልጻ፤ ይህ ተግባር በሌሎቹ ወራትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆን አለበት ብላለች። 


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም