ቀጥታ፡

በወላይታ ዞን በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የምርጫ አዋጅ ጥሰት የፈጸሙ 93 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2015(ኢዜአ)፦ በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በወላይታ ዞን የምርጫ አዋጅ ጥሰት የፈጸሙ 93 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋለቸውን የፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሕዝበ ውሳኔ መካሄዱ ይታወቃል፡፡

ኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ ዞኖች እንዲሁም በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአሌ፣ በአማሮ፣ በዲራሼ ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔው ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት ይፋ ሲያደርግም ከምርጫ አዋጅ ጥሰት ጋር በተያያዘ የወላይታ ዞን የህዝበ ውሳኔ ውጤትን እንዳላጸደቀው ይታወቃል፡፡

ቦርዱ በወላይታ ዞን የተደረገው ሕዝበ ውሣኔ የሂደቱን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሁኔታ መፈጠሩንና በምርጫ ሕጉና አግባብነት ባላቸው መመሪያዎች መሠረት እንደ ከባድ የአሠራር ጥሠት የሚቆጠሩ ተግባራት በመገኘታቸው ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።

በዚህ መሰረት የፍትህ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በዞኑ የምርጫ አዋጅ ጥሰት የፈጸሙ 93 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።


 

የፍትህ ሚኒስቴር ዴኤታ ፍቃዱ ጸጋ እና በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን መመሪያ ሀላፊ ሙሊሳ አብዲሳ በጋራ በሰጡት መግለጫ በወላይታ ዞን የተፈጸመውን የምርጫ አዋጅ ጥሰት ላይ የተደረገውን ምርመራ ውጤት ይፋ አድርገዋል።

በዚህ መሰረት የፍትህ ሚኒስቴር፣የፌደራል ፓሊስ፣ የክልል ፖሊስና አቃቢ ህግ ከምርጫ ቦርድ የቀረበውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ምርመራ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የተቋቋመው የምርመራ ቡድን ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ ለማጣራት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህ መሰረት 451 ከሚሆኑ የተለያዩ ግለሰቦች ቃል በመቀበል 136 ተጠርጣሪዎችን የመለየት ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 18ቱ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመው 118 የሚሆኑት ደግሞ የምርጫ አስፈጻሚዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም 93 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው ቀሪዎቹ 45 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም