የዒድ አልፈጥር በዓል ስናከብር በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል - ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
የዒድ አልፈጥር በዓል ስናከብር በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል - ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 12/2015 (ኢዜአ) ፦ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የዒድ አልፈጥር በዓል ጨረቃ ዛሬ ማታ ከታየች ነገ አርብ ፤ ካልታየች ደግሞ ቅዳሜ እንደሚከበርም ነው የተገለጸው፡፡
የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዒድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የመተዛዘን እና የመረዳዳት እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የረመዷን ወርን አስመልክቶ በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ የጎዳ ላይ ኢፍጣር መርሐግብሮች ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በታላቁ የረመዷን ወር መጨረሻ የሚከበረውን የዒድ አልፈጥር በዓልን በሰላምና በመተሳሰብ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ማሳለፍ እንደሚገባም ፕሬዚደንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡