ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 12/2015(ኢዜአ):-በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሁለተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።
ኢትዮጵያ መድን ከመቻል ከቀኑ 9 ሰአት ይጫወታሉ።
በደረጃ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ መድን በ37 ነጥብ 3ኛ እንዲሁም መቻል በ23 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ መድን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ አሸንፏል ፤አንድ ጊዜ ተሸንፏል ፤ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።
በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሐ-ግብር ሁለቱ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የ20ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ-ግብር ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በ27 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሀዲያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።
ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
አንድ ጊዜ ተሸንፏል አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ20ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲን 3 ለ 1 ሲያሸንፍ አርባ ምንጭ ከተማና ኢትዮጵያ ቡና ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።