ፍቼ ጨምባላላ በውስጡ የያዛቸው ዕሴቶች ለትውልዱ የአብሮነትና ፍቅር ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው - ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ፍቼ ጨምባላላ በውስጡ የያዛቸው ዕሴቶች ለትውልዱ የአብሮነትና ፍቅር ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው - ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ሚያዝያ 11/2015 (ኢዜአ)፡- የፍቼ ጨምባላላ በዓል በውስጡ የያዛቸው እሴቶች ለትውልዱ የአብሮነትና ፍቅር ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ ።
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምባላላ የዋዜማ ክብረ በዓል "ፊጣራ" በሀዋሳ እየተከበረ ይገኛል ።
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት የ"ፍቼ ጨምባላላ" በዓል በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውና በርካታ ማህበረሰባዊ ጠቀሜታ ያላቸው ኩነቶች የሚከወኑበት ነው ።
"በዓሉ በውስጡ የያዛቸው እሴቶች ለአሁኑ ትውልድ የአብሮነት፣ የፍቅርና የወንድማማችነት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው" ብለዋል ።
በአሉ ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገሪያ በዓል እንደመሆኑ በሲዳማ ህዝብ ዘንድ የአቀባበል ዝግጅት የሚጀመረው ከወራት በፊት እንደሆነ አስረድተዋል ።
በተለይ የባህል አባቶች የሆኑ "ሞቴ" እና "አያንቱዎች ፍቼ ጨምባላላ ከመድረሱ በፊት የሚያከናውኗቸው ሥርዐቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እንደሆነ ገልፀዋል።
ከእነዚህ ክንውኖች መካከል "ኡሱራ" የተሰኘው ሥርዓት ወደ አዲሱ ዓመት ከመሸጋገራቸው በፊት ያለፈውን ዓመት ክፋትና በጎ ያልሆነ ነገር ለማስቀረት ፈጣሪን ይቅርታ የሚለምኑበት እንዲሁም በፍጹምና ቅን ልቦና ከርሱ ጋር ዕርቅ የሚያደርጉበት እንደሆነ ገልፀዋል ።
ይህን ተከትሎ ሁሉም ህዝብ ያለፈውን ዓመት ቂም በቀል በዕርቀ ሰላም በማስወገድ " ሁሉቃ " የተሰኘውን የመሽሎክና የመሻገር ሥርዐት የሚያካሂድ እንደሆነም ጠቅሰዋል ።
"በዚህም ዕርቅ፣ ሠላም፣ ይቅር ባይነት፣ ፍቅር፣ አንድነትና ወንድማማችነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር ቆይቷል" ብለዋል።
ለበዓሉ ሁሉም እንዳቅሙ ሁለንተናዊ ዝግጅት እንደሚያደርግ ገልፀው የሌለው አዲሱን ዓመት በመከፋት እንዳይቀበል በመሰብሰብ በጋራ ተደስተው የሚያከብሩት ትልቅ የመደጋገፍ እሴት ያለው በዓል እንደሆነም ተናግረዋል ።
ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በጋራ የሚከበር መሆኑም በህዝቦች መካከል ወንድማማችነትን በማስረፅ የሚያበረክተው አስተዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል ።
የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ የሆው የ'ፍቼ ጨምባላላ" በዓል የዋዜማው "ፊጣራ" ስርዓት በተለያዩ ክዋኔዎች የፌደራልና ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች በተገኙበት በመከበር ላይ ነው።
በዓሉን ለመታደም ሀዋሳ ከተማ ከገቡት ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ይገኙበታል።
ከፍተኛ አመራሮቹ ሀዋሳ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና በትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሳ፣ በክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ እና በሌሎች የክልሉ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።