የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች በትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፋቸው ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እድገት እያገዘ ነው--የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች በትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፋቸው ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እድገት እያገዘ ነው--የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
ባህር ዳር ሚያዚያ 11/2015(ኢዜአ)፦ የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች በትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ላይ መሳተፋቸው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እድገት እንዲፋጠን እያገዘ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ብሩክ አዳነ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ መንግስት የቀረፀው የአገር በቀል ኢኮኖሚ እንዲሳካ የመንገድ ዘርፉ ወሳኝ ሚና አለው።
መንገድ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብና የህብረተሰቡን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማሳለጥ ያለውን ጥቅም በመገንዘብ በስፋት እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በሀገሪቱ ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች በአብዛኛው በውጭ የሥራ ተቋራጮች ይገነቡ እንደነበር አስታውሰው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ አቅም ባላቸው የሃገር ውስጥ የመንገድ ሥራ ተቋራጮች በጥራት እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በሰሜን እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከሚገነቡ ስምንት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ብቻ በውጭ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት እየተገነባ መሆኑን ኢንጂነር ብሩክ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በተለይ ከዳባት-አጅሬ- ቅራቅር-ከተማ ንጉስ እና ከበለስ-መካነ ብርሃን እየተገነቡ የሚገኙት የ139 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታዎች ተጨባጭ መሳያዎች መሆናቸውን ነው የገለጹት።
"የአካባቢው መልክአ ምድር አስቸጋሪ ቢሆንም በመንገድ ግንባታ ሥራው የአገር ውስጥ ተቋራጮች ችግሩን ተቋቁመው ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ" ብለዋል።
ይህም እስካሁን በነበረው የመንገድ ግንባታ ሥራ የአገር ውስጥ ተቋራጮች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የራሳቸውን አቅም ስለመገንባታቸው ያረጋገጠ ነው ሲሉም አክለዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በአገር ውስጥ ተቋራጮች መገንባታቸው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እድገት እንዲፋጠን ከማገዝ ባለፈ ለውጭ ተቋራጮች ይከፈል የነበረን በውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል።
ኢንጂነር ብሩክ አክለውም የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች እየበዙና አቅማቸው እያደገ በመጣ ቁጥር እርስ በርስ መደጋገፍና አዎንታዊ ፉክክር በመፍጠር ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲከናወኑ ያደርጋል።
"በአሁኑ ወቅት በትልልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሳይቀር የአገር ውስጥ ተቋራጮች መሳተፋቸው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉ ትልቅ ለውጥ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሰሎሞን ደመቀ በበኩላቸው "ኢንተርፕራይዙ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች መንገድ በመገንባት ዘርፉን እያገዘ ነው" ብለዋል።
በተለይም በሌሎች ሥራ ተቋራጮች ሊደፈሩ የማይችሉ ሥራዎች ሲያጋጥሙ ኢንተርፕራይዙ መንገዱን በጥራትና በፍጥነት ሰርቶ በማስረከብ አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ እውቀቶችን እና አሰራሮችን ለሌሎች አገር በቀል ተቋራጮች በማስተዋወቅና በማስተላለፍ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ኢንተርፕራይዙ በስፋት እያካሄደ ያለውን የመንገድ ግንባታ በቀጣይም አጠናክሮ በማስቀጠል ሀገራዊ ልማትን ከፊት ሆኖ ለማገዝ መዘጋጀቱንም ኢንጂነር ሰሎሞን አረጋግጥዋል።
መንግስት የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ተጠናክረው ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።