የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሰራሩን በማዘመን በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተደራሽነት አድማሱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሰራሩን በማዘመን በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተደራሽነት አድማሱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 11/2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሰራሩን በማዘመን በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተደራሽነት አድማሱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ከተቋቋመ 80 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ አስተማማኝና ተጽእኖ ፈጣሪ የመረጃ ምንጭ የመሆን ግብን አስቀምጦ ይህን የሚመጥን የሪፎርም ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
ተቋሙ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት ባደረገው ስምምነት መሰረትም በየኒቨርሲቲው የበለጸገና "የተቀናጀ የዲጂታል ዳታ አስተዳደር ስርዓት " የተሰኘ መተግበሪያን በሙከራ ደረጃ ዛሬ ጀምሯል፡፡
መተግበሪያው የተቋሙን የመረጃ አያያዝ ስርዓት ከማዘመን ባለፈ መገናኛ ብዙሃን ጋር በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢዜአ ከአገር አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ የመረጃ ምንጭ የመሆን ራዕይ አንግቦ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ይህን ለማሳካትም በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው መተግበሪያ መረጃዎች በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆኑ እና በአግባቡ ተቀምጠው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
መረጃዎች ከተለያየ ቦታ በፍጥነት ወደ ማዕከል እንዲደርሱና ለመገናኛ ብዙሃንም ተደራሽ እንዲሆኑ ጭምር የሚያግዝ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ይህም ተቋሙ ያስቀመጠውን ግብ እውን እንዲሆን በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ዶክተር ድሪባ ኢቲቻ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲዘምን የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።
በኢዜአ በሙከራ ደረጃ የተተገበረው "የተቀናጀ የዲጂታል ዳታ አስተዳደር ስርዓት" የዚሁ ስራ አካል እንደሆነም ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ዶክተር ወርቁ ጂፋራ በበኩላቸው መተግበሪያው ኢዜአ ከተለያዩ ቅርንጫፎቹ መረጃዎችን በፍጥነት እንዲለዋወጥ ያግዛል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሲሰራበት የነበረውን ስርዓት በማዘመን ተቋሙ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የያዘውን የሪፎርም ስራ ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዲጂታል ዳታ ማዕከል ኃላፊ አቶ ሄኖክ ታደሰ መተግበሪያው ኢዜአ ካሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች የድምጽና የምስል ግብዓቶችን በፍጥነት ለመቀበል እንዲሁም ዜናና ዜና ነክ ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ አመልክተዋል፡፡
ምስሎች እንዳይባክኑም የራሱ ሆነ የመቆጣጠሪያ ስርዓት እንደተዘጋጀለትም ጠቁመዋል።