ቀጥታ፡

በ"ስቶፕ ኦቨር አዲስ" አገልግሎት አማካኝነት በርካታ የውጭ ሀገራት መንገደኞች አዲስ አበባን እንዲጎበኙ በቅንጅት እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ አየር መንገድ

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 11/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ"ስቶፕ ኦቨር አዲስ" አገልግሎት አማካኝነት በርካታ የውጭ ሀገራት መንገደኞች አዲስ አበባን እንዲጎበኙ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ መንገደኞችን በማጓጓዝ የአፍሪካ ኩራት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው አየር መንገዱ የሚያመላልሳቸው አብዛኛዎቹ መንገደኞች አዲስ አበባን መሻገሪያቸው በማድረግ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚጓዙ ናቸው።

አየር መንገዱ መንገደኞች እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሙባትን አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2018 ጀምሮ ''ስቶፕ ኦቨር አዲስ ''የተሰኘ የመንገደኞች ጥቅል አገልግሎት አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ በመቀዛቀዙ አገልግሎቱ በሚፈለገው ደረጃ ገቢራዊ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡

አሁን ላይ የሰላም ስምምነቱና በኮቪድ-19 ተጥለው የነበሩ የጉዞ እገዳዎች መነሳታቸውን ተከትሎ የቱሪስት ፍሰቱ ወደ ነበረበት እየተመለሰ ይገኛል።

በመሆኑም በ''ስቶፕ ኦቨር አዲስ'' ጥቅል አገልግሎት አማካኝነት በርካታ የውጭ አገራት መንገደኞች አዲስ አበባን እንዲጎበኙ እየተሰራ ስለመሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም በዛሬው እለት በጥቅል አገልግሎት አማካኝነት ከኢንዶኔዥያ ጃካርታ በመነሳት በአዲስ አበባ አድርገው ወደ ሶስተኛ ሀገር የሚጓዙ ከመቶ በላይ መንገደኞች ለሰዓታት በሚኖራቸው ቆይታ አዲስ አበባን እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡

በቆይታቸውም እንጦጦ ፓርክ ፣ወዳጅነት ፓርክና መሰል የቱሪዝም መስህቦችን ጎብኝተው ወደ  መዳረሻ ሀገር እንደሚጓዙ ነው የተገለጸው፡፡


 

መንገደኞቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ሆሊ ዴይስ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ማህሌት ከበደ ከቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ጋር በመሆን አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ዳይሬክተሯ ማህሌት ከበደ በዚሁ ጊዜ፤ አየር መንገዱ በ "ስቶፕ ኦቨር አዲስ'' ጥቅል አማካኝነት በርካታ ጎብኚዎች አዲስ አበባን እንዲጎበኙ እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከባለድርሻ ተቋማት ጋር  በመሆን ኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ አየር መንገዱ ያለውን አጋጣሚ በመጠቀም የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል። 


 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቱሪስቶች ኢትዮጵያንን እንዲጎበኙ ለማድረግ እቅድ መቀመጡን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት 700 ሺህ ቱሪስቶች ሀገሪቱን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል። 

ከዚህ አኳያ አየር መንገዱ የጀመረው ተግባር ለዘርፉ መነቃቃት ሚናው የጎላ መሆኑን ነው  የተናገሩት፡፡

መንግስት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን  በማንሳት በቀጣይም የቱሪዝም ሚኒስቴር ከአየር መንገዱና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ዘርፉን ለማነቃቃት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡


 

ከኢንዶኔዥያ ጃካርታ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገቡት ጎብኚዎች በበኩላቸው ስለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት እድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።


 

በቆይታቸውም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆኑ ባህል፣ ወግና የምግብ ስርዓት ለማየት ጉጉት እንዳደረባቸው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም