ቀጥታ ስርጭት

"በወርልድ ቴኳንዶ ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ለማፍራት ደረጃውን የጠበቀ ሁለገብ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ያስፈልጋል" - ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ

 በኢትዮጵያ በሕጻናት፣ወጣቶችና አዋቂዎች በስፋት ከሚዘወተሩ የስፖርት አይነቶች አንዱ ወርልድ ቴኳንዶ ነው።

ስፖርቱ እንደ አገር ከሚያበረከተው አስተዋጽኦ አንጻር ተገቢውን ትኩረት አግኝቷል ማለት እንደማይቻልና በተለይም የመለማመጃ ቦታ ችግር ለእድገቱ ማነቆ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የወርልድ ቴኳንዶ ነባራዊ ሁኔታ፣ ስፖርቱን ለማሳደግ መስራት ስለሚገባቸው ጉዳዮችና ተያያዥ ሀሳቦች በተመለከተ ኢዜአ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ከሆኑት ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኢዜአ-  የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት  እያደገ  ተዘውታሪነቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉ፣ አንተም ረጅም ጊዜ የቆየህበት ስፖርት እንደመሆኑ በእርግጥ ስፖርቱ እያደገ ነው ማለት ይቻላል ?

ማስተር አዲሱ - ስፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ እያደገ ነው ማለት አይቻልም።በአገራችን ብዙ ማሰልጠኛ ማዕከላት አሉ። ከሕጻንነት እድሜ ጀምሮ የሚሰሩ በጣም ብዙ ልጆች አሉ፤ግን እንደ ክለብ ተወዳዳሪ ክለቦችን እስካሁን አልተቋቋሙም፤ ይህም ደግሞ ብዙ ተጫዋቾች እንደ ልብ እንዳይፈሩ እያደረገ ነው። ከማሰልጠኛ ማዕከላት ወደ ክለቦች የሚቀላቀሉበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ነው።ይህም ልጆቹ ነገ ላይ አገራቸውን በተለያዩ ውድድሮች በመወከል ለመሳተፍና ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚችሉበት ሁኔታ ላይ የተሻለ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ፌዴሬሽኑ በዚህ ላይ ጠንክሮ መስራት አለበት።

ኢዜአ - አሁን ላይ እንደ አገር ምን ያህል ማሰልጠኛ ማዕከላትና ስፖርተኞች አሉ ?

ማስተር አዲሱ- በወርልድ ቴኮንዶ 10 ሺህ በላይ ክለባት ወይም ማሰልጠኛ ማዕከላት አሉ እነዚህ ሕጋዊ የሆኑ ክለቦች ናቸው እንጂ ያልተመዘገቡና ስልጠና የሚሰጡ ማዕከላት ይኖራሉ። እነዚህ ክለቦች በጣም ብዙ ሕጻናት ወጣቶች እንዲሁም አዋቂዎችን በስፖርት ብቁ የማድረግ ጤናማ ማህበረሰብ እየፈጠሩ ነው የሚገኙት።በእነዚህ ማሰልጠኛ ማዕከላት በአማካይ እስከ 80 ሰልጣኞች ይኖራቸዋል።ይህም በስራቸው በርካታ ስፖርተኞች አቅፈው ይዘዋል ማለት ነው።

ኢዜአ -ስፖርቱ እንደ አገር ሆነ እንደ ማህበረሰብ ምን አይነት ጠቀሜታ አለው ?

ማስተር አዲሱ - አንድ የቴኳንዶ ተማሪ በጣም ዲሲፒሊንድ ነው ፤ አገሩን የሚወድ ነው ፤ሰው አክባሪ ነው፣ ታታሪ ሰራተኛም ነው የሚሆነው ።ይህን ደግሞ ለቤተሰብም ሆነ ለአገር እድገትና ሰላም ወዳድ ዜጋ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ኢዜአ- ስፖርት ለአገር ሰላም የራሱ አስተዋጽእ እንዳለው ይታወቃል፤ የቴኳንዶ ስፖርት በተለየ መልኩ ከሰላም ጋር ምን አይነት ቁርኝት አለው ?

ማስተር አዲሱ- ስፖርቱ  የመጀመሪያው ጉዳይ ሰላምን ነው የሚያስተምረው ከ11 የቴኳንዶ ሕጎች አንዱ አገርህን፣ወዳጆችን፣ጓደኞችህን አክብር ውደድ ነው የሚለው። ስለዚህ የቴኳንዶ ስፖርት ለአገር ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።ይህ መርህ ደግሞ የዕለት ከዕለት ሕይወት ውስጥ አብሮ ይዋሃድና እንደ አገር ሰላም ወዳድ ሕብረተሰብ ይፈጥራል።

ኢዜአ- ስፖርቱ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው ?

ማስተር አዲሱ- በአገራችን አሰልጣኞች ለስፖርተኞች ስልጠናዎችን  የሚሰጡበት ቦታ በብዛት ወጣት ማዕከላት ውስጥ ነው ።እሱ ብዙ የተመቻች አይደለም ፤የግለሰብ ቤት ተከራይተው የሚሰሩም ቢኖሩም  ኪራዩ  ስለሚወደድባቸው  በጣም ይቸገራሉ፤ እሱ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ቡድኑ በዝግጅት ወቅት ልምምድ የሚሰራበት የራሱ ጂም የለውም፤ እየለመንን በተለያዩ ቦታዎች ነው የምንሰራው። ይህን የማመቻቸት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፤ ስፖርቱን የሚመራው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የብሔራዊ ቡድን የሚዘጋጁበት ቦታ ማመቻቸት አለባቸው። ስፖርቱ አሁን ላይ አገርን ወክሎ ኦሊምፒክ ላይ ድረስ መሳተፍ የቻልንበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፤ ግን ስፖርቱ የተሻለ ተሳትፎና ውጤት እንዲኖረው የመለማመጃ ቦታ መክፈት ይገባል የሚል ሀሳብ አለኝ። አሁን ላይ ለየትኛው ስፖርት ደረጃውን የጠበቀ ሁለገብ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ የለም።ይህ ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። ስለዚህ በወርልድ ቴኳንዶ ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ለማፍራት ደረጃውን የጠበቀ ሁለገብ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ያስፈልጋል። 

ኢዜአ- የግል ተቋማትና ድርጅቶች በዚህ ስፖርት ማደግ ምን ሚና አላቸው  ?

ማስተር አዲሱ - ወደ ፊት እንደ አገር ከፍ ያለ ውጤት ልናመጣበት የምንችልበትና  የኦሊምፒክ ስፖርትም ጭምር  ስለሆነ የግል ካምፓኒዎች ስፖርቱን ክለብ በመያዝ መደገፍ ይችላሉ። በተለይ እንደ ቴሌ፣ባንክ፣አየር መንገድ አይነቶቹ ትንሽ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ይዘው ቢሰሩ ውጤታማ መሆን የሚችሉ ታዳጊዎች ማፍራት ይቻላል።

ኢዜአ -በቀጣዮ እኤአ በ2024 በፓሪስ በሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ በወርልድ ቴኳንዶ ከባለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክ አንጻር ያለው የዝግጅት ጊዜ አያጥርም ? 

ማስተር አዲሱ- ከቶኪዮ 2020 በኋላ ብሔራዊ ቡድኑ ፈርሶ ነበር። አሁን ላይ ለቀጣዩ ኦሊምፒክ ኳሊፊኬሽን የቀረው 11 ወራት አካባቢ ነው ፤አሁን በቅርቡ ግን የብሔራዊ ቡድን ለማቋቋም ምርጫ ተደርጓል ።ነገር ግን ለኦሊምፒኩ የዝግጅት ጊዜ ከባለፈው ኦሊምፒክ አንጻር ሲታይ በጣም ዘግይቷል፤ ባለፈው አትሌት ሰለሞን በተሳተፈበት የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ አራት ዓመት ሙሉ ነበር ፌዴሬሽኑ ዝግጅት ያደረገው። አሁን ግን የቀረን 11 ወራት ያህል ጊዜ ነው። በቀረው አጭር ጊዜ የተሟላ ዝግጅት ለማድረግ ጊዜው አጭር ነው፤ ያም ሆኖ ጥሩ ውጤት ለማምጣት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።  

ኢዜአ- ለነበረን ቆይታ አመስግናለሁ

ማስተር አዲሱ- እኔም አመሰግናለሁ

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም