ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለሕዳሴው ግድብ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር  ድጋፍ ተሰበሰበ

ድሬዳዋ ሚያዝያ 11/2015 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን የድሬዳዋ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተያየት የሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ተቋማት እና ባለሀብቶች ከ96 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢ እና በስጦታ ለግድቡ ድጋፍ አድርገዋል።

የድሬዳዋ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤትኃላፊ አቶ ሀብታሙ አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአስተዳደሩ የገጠር እና የከተማ ነዋሪዎች በቦንድ ግዢ እና በስጦታ እያበረከቱት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል።

ዘንድሮም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከባለሀብቶች፣ ከሠራተኞችና ከተቋማት 25 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታሶቦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል። 

አቶ ሀብታሙ እንዳሉት የታሰበውን ዕቅድ ለማሳካት ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ድረስ የሚቆይ የቦንድ ሽያጭ እየተከናወነ ይገኛል።

በእዚህም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ በሁሉም ተቋማት እና አደረጃጀቶች በህዝባዊ ንቅናቄ የታጀበ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ ከ90 በመቶ በላይ የተገባደደው የሕዳሴው ግድብ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማስፋፋት ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ለግድቡ በቦንድ ግዢ ላይ የተሳተፉትና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ለሕዳሴው ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ አጠናክረው ይቀጥላሉ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ደሳለኝ ኦልጅራ በበኩላቸው ግድቡ የአገርን ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በራሳቸውና በቤተሰባቸው አባላት ለተከታታይ ዓመታት ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል። 

ቦንድ ገዝተው የተመለሰላቸው ገንዘብ የቁጠባ ባህልን እንዲያዳብሩ ያገዛቸው መሆኑን ጠቁመው፣ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቅ ድረስ ድጋፍቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ተስፋ ለሆነው የሕዳሴው ግድብ ያለቀስቃሽ የሚያደርጉትን ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያጠናክሩ የገለጹት ደግሞ አቶ ጋሻው ስዩም የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

"የግድቡን ግንባታ በአንድነት እንደጀመር ነው ሁሉ ተረባርበን ለመጨረስ በተለያየ መንገድ ስናደርገው የነበረውን ተሳትፎ ማጠናከር አለብን" ብለዋል።

የመንግስት ሠራተኛው አቶ ባንተጊዜ ቸኮል በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ የሚያፋጥንና የዜጎችን ተስፋ የሚያለመልም በመሆኑ እስከመጨረሻው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም