ቀጥታ፡

የፊቼ ጨምባላላ በዓል ሲከበር ያለፈውን ቁርሾ በመተውና ጥላቻን በማስወገድ ሊሆን ይገባል- የሲዳማ ክልል 

ሀዋሳ ሚያዚያ 11 / 2015 (ኢዜአ):- የፊቼ ጨምባላላ በዓል ሲከበር ያለፈውን ቁርሾ በመተውና ጥላቻን በማስወገድ ሊሆን እንደሚገባ የሲዳማ ክልል አስታወቀ።

የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው የጨምባላላ በዓል ነገ በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የበዓሉ ማክበሪያ ስፍራ ጉዱማሌ ይከበራል።

የክልሉ መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ፊልጲዮስ ናሆም፤ በዓሉን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግስት በዓሉ በሰላም እንዲከብር የጸጥታ ሃይሉና ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት  የቅድመ ዝግጅት ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

ዛሬ በበዓሉ ዋዜማ የፊቼ ጨምባላላ ያሉት ዕሴቶች የሚያሳይ ሲምፖዚየም እንደሚካሄድና የሻፌታ የሲዳማ ባህላዊ ምግብ የመቋደስ ባህላዊ ስርዓት ፊጣራ ስርዓት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

"የፊቼ ጫምባላላ በዓል ለስነ-ክዋክብት ምርምር ትልቅ አሻራ ማኖር የሚችል ነው" ብለዋል።

የቀለም ትምህርት ጥበብ ባልነበረበት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የረቀቀ የሳይንስ ሂደት ባልነበረበት ከጥንት ጀምሮ የጨረቃና የከዋክብት ዑደትን በመመልከት አባቶች የዘመን አቆጣጠር ቀመርን በማጤን ዕለቱን ይለዩ እንደነበር ነው ፊልጲዮስ ያወሱት።

ይህም የአባቶችን ድንቅ ጥበብና እምቅ ዕውቀት የሚያሳይ በዓል መሆን የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል።

ፊቼ ጫምባላላ በውስጡ የያዛቸው የፍቅር፣ አብሮነትና ሰላም እሴቶችን ለአሁናዊ አገራዊ ሁኔታና ለዓለም አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

"በበዓሉ የተጣላ ሳይታረቅ፣ የተቀያየሙ ይቅርታ ሳይጠያየቁና የጥላቻን ግድግዳ ንደው በፍቅር ሳይደምቁ ማክበር የማይታሰብ ነው" ሲሉ አቶ ፊልጲዮስ የተናገሩት።

ፊቼ ጫምባላላ የአብሮነት በዓል በመሆኑ መገፋፋት ሳይኖር ያለው የሌለውን የሚረዳበት መሆኑንና 

ይህም ልዩነትን በመቀነስ የሚያስተሳስር መቀራረብ፣መተባበርና በጋራ መቆምን የሚያስተምር መሆኑን ነው ያብራሩት።

ይህም አንድነት ኃይል መሆኑንና እውነተኛ ፍቅር አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ በዓል እንደሆነ ገልጸዋል።

በዓሉ ከመድረሱ አስቀድመው አባቶች ለአገር አንድነትና አብሮነት መጽናት በደል እንዲሻር ልምላሜና ብልጽግና እንዲመጣ እንዲሁም አዲሱ ዓመት የተስፋና የስኬት እንዲሆን በመጾምና በመጸለይ ወደ ፈጣሪያቸው ይማጸናሉ ብለዋል።

ስለሆነም በዓሉ ሲከብር ያለፈውን ቁርሾ በመተው፣ ጥላቻን በማስወገድ ኢትዮጵያዊ ፍቅር በመግለጽ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

"ለኢትዮጵያ ሰላምና ለምንመኛት ኢትዮጵያ ግንባታ ሰላምና ፍቅር ወሳኝ በመሆኑ ሁላችንም በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ መነሳት አለብን" ነው ያሉት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው።

የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የፊቼ-ጫምባላላ በዓልን ለመጪው ትውልድ ለማሸጋገር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጭሪ አቅርበዋል።

አቶ ፊልጲዮስ የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች በሙሉ እንኳን ለ2015 ዓ.ም የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በሚል የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም