ቀጥታ፡

የፊቼ ጫምባላላ በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል--- ኮሚሽኑ

ሐዋሳ (ኢዜአ) ሚያዚያ 10/2015 የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ" በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ ለኢዜአ እንደገለጹት የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ባለድርሻ አካላት የጋራ ዕቅድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው።

በዚህም በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። 

"ህዝባዊ በዓላት ሲከበሩ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ይገባል" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በዓሉ ከሃዋሳ በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች ስለሚከበር ዝግጅቱ ይህንን ታሳቢ ማድረጉን ገልጸዋል። 

ለበዓሉ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች የሚመጡ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከህብረተሰቡ ጋር የተደረገውን ውይይት መነሻ በማድረግ ትኩረት የሚሹ አካባቢዎች ተለይተው ተገቢ ክትትል እንደሚደረግባቸውም ኮሚሽነር ሽመልስ አመልክተዋል። 

በሀዋሳ ከተማ የተተከሉ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎች በመታገዝ ከአንድ ማዕከል የሚደረግ ክትትልም ወንጀልን ለመከላከል ለተሰማራው የጸጥታ ኃይል እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

እንዲሁም ሌሎች ተንቀሳቃሽ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎች የበዓሉን ታዳሚ ደህንነት ለመጠበቅ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ነው ኮሚሽነር ሽመልስ ያስታወቁት።

"የአካባቢው ወጣቶችም በሰላም አምባሳደርነት ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የሰላምና ጸጥታውን ሥራ ያከናውናሉ" ብለዋል። 

በተጨማሪም ከሃገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዓሉን በሰላም ለማክበር የሚያስችል ውይይት መደረጉን ኮሚሽነር ሽመልስ ገልጸዋል።

በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ እንዲቻል ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በከተማው ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች መጠቀም እንደማይቻልም ኮሚሽነር ሽመልስ አስታውቀዋል።

"በዓሉ በሚከበርበት ቀን ደግሞ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በከተማው አገልግሎት እንዳይሰጡ ክልከላ ተጥሏል" ብለዋል።

በበዓሉ ወቅት ለሚፈጠሩ ወንጀሎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ ሁለት ተንቀሳቃሽ ችሎቶች መቋቋማቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ህብረተሰቡ ለሰላም ስጋት የሆነ ነገር ሲመለከት በ0462209164 ጥቆማ እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም