ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኮሪያ የኢንቨስትመንት ፎረም ተጀመረ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2015(ኢዜአ):- የ2023 ኢትዮ-ኮሪያ የኢንቨስትመንት ፎረም በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተማ ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በፎረሙ ላይ ከ120 በላይ የኮሪያ ባለሃብቶችና የድርጅት ኃላፊዎች ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል።

ፎረሙ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት እድሎችና አማራጮች ለኮሪያ ኢንቨስተሮች ማሳወቅ ያለመ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነትና መልካም ወዳጅነታቸው በኢኮኖሚ ዘርፍ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች የተዘጋጁ ተለያዩ ማበረታቻ ማዕቀፎች፣በመንግስት የተወሰዱ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምቹነት እንዲሁም የመሰረተ ልማት እድገት መጨመር ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች ተመራጭ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ በኢትዮጵያ ስላሉ ዘርፈ ብዙ የኢንቨትመንት እድልና አማራጮች፣አገራዊ የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ስራዎች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ምቹ በመሆኑ የኮሪያ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ምቹ ጊዜ ነው ብለዋል።

የኮሪያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ፌዴሬሽን ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጁ ሶርዮንግ የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያ ታሪካዊ የሆነ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው አውስተዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ያለውን ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም እንደሚገነዘብና ሁለቱንም አገሮች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እድሎቹን ለመጠቀም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

የ2023 ኢትዮ-ኮሪያ የኢንቨስትመንት ፎረም በቀጣይ ቀናትም እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም