ቀጥታ፡

13ተኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ ምርቶች የንግድ አውድ ርዕይ  በአዲስ አበባ ይካሄዳል 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 10/2015 (ኢዜአ) 13ተኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ የንግድ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከሚያዚያ 12 እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር አስታወቀ።

ማህበሩ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዳስትሪ ልማት ድርጅትና ሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር አውደ ርዕዩን እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሬድማን በዳዳ እንደተናገሩት፤ አውደ ርዕዩ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያገናኝና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ነው።

እንዲሁም በኮቪድ- 19 እና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የተቀዛቀዘውን የቆዳውን ዘርፍ ለማነቃቃት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ሃብት ቢኖራትም በዘርፉ ላይ የሚታዩ የምርት አያያዝ እና የግብይት ሥርዓት ተግዳሮቶች ዘርፉ በሚገባው ልክ አስተዋፅኦ እንዳይወጣ አድርጎታል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ 13ተኛው የቆዳ ምርቶች የንግድ አውደ ርዕይ የገበያ ትስስር ለማስፋት ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የማህበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን ጌቱ፣ የቆዳ ንግድ አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ካላት የቆዳና ሌጦ ሃብት አኳያ ብዙ ያልሰራችበትን የፋሽን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

በንግድ አውደ ርዕዩ ከ200 በላይ የተለያዩ ሀገራት የቆዳ ውጤቶች አምራቾች፣ የማሺነሪዎችና ግብዓት አቅራቢዎች፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም