ቀጥታ፡

ማህበሩ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በድርቅ እና በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

ጂንካ  ሚያዚያ10/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በደቡብ ኦሞና በኮንሶ ዞኖች በድርቅና በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ቢሻው እንዳሉት ጽህፈት ቤቱ በአካባቢው በድርቅና በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ማህበሩ ከሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የተለያዩ አጋር አካላትን በማስተባበር ባገኘው ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በደቡብ ኦሞና በኮንሶ ዞኖች በጎርፍና በድርቅ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ትናትና ዛሬ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በድጋፉም በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች፣ ሐመር፣ ባካ ዳውላ አሪ እና በና ጸማይ ወረዳዎች በድርቅና በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ1ሺህ 900 በላይ አባውራዎች የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ 350 ኩንታል የምግብ ዱቄት፣ ዘይት፣ ብርድ ልብስ፣ መጠለያ ሸራ እና ሌሎች የቤት መገልገያ ቁሶችን ማካተቱንም ጠቁመዋል።

በኮንሶ ዞን በተከሰተ ድርቅ ለጉዳት ለተዳረጉ 50 አባውራዎችም ለእያንዳንዳቸው ብርድልብስ እና ለመኖሪያ ቤት የሚሆን ሸራ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ መደገፉን አቶ ጥላሁን አመልክተዋል።

በሐመር ወረዳ የተደረገውን የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ የተረከቡት የወረዳው አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባደገ ጥላሁን፤ ማህበሩ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በአካባቢው በተከሰተ ድርቅ ምክንያት በርካታ የቤት እንስሳት መሞታቸውን አስታውሰው፣ "ድርቁ በሰብል ላይም ጉዳት በማድረሱ በርካታ አርብቶ አደሮችም ተረጂ ሆነዋል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየጣለ ያለው ዝናብ መልካም አጋጣሚ ቢፈጥርም ድርቁ ካስከተለው መጠነ ሰፊ ቀውስ ለማገገም ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ ባደገ ገልጸዋል።

ማህበር ድጋፍ ካደረገላቸው የሐመር ወረዳ አስሌ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ላሌ ጊላ ለተደረገላቸው  ድጋፍ አመስግነዋል።

በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በርካታ የቤት እንስሳት እንደሞቱባቸው ተናግረው፣ በዚህም ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መጋለጣቸውን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በመንግስትና በረድኤት ድርጅቶች እየቀረበ ያለው ለእንስሳት ሕክምና የሚሆን ግብአት እና የተጎጂዎች ቀለብ እንዲጠናከር ጠይቀዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም