በኢትዮጵያ የተከሰቱ በደሎችን በተጠያቂነት መርህ በሽግግር ፍትህ በእርቅና ይቅርታ ለመቋጨት የሚደረገውን ጥረት እናግዛለን- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተከሰቱ በደሎችን በተጠያቂነት መርህ በሽግግር ፍትህ በእርቅና ይቅርታ ለመቋጨት የሚደረገውን ጥረት እናግዛለን- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት
አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/ 2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የተከሰቱ በደሎችን፣ ቁርሾና ኢ-ፍትሐዊነትን በተጠያቂነት መርህ በሽግግር ፍትህ በእርቅና ይቅርታ ለመቋጨት ለሚደረገው ጥረት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ።
በፕሪቶሪያ መንግስትና ህወሃት ያደረጉትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
የመልሶ ግንባታ፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ስራ ማስጀመርና ሌሎችንም መሰረታዊ ስራዎች የማከናወን ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በኢትዮጵያ የተከሰቱ በደሎችን፣ ቁርሾና ኢ-ፍትሐዊነትን በተጠያቂነት መርህ በእርቅና ይቅርታ መፍትሔ ለመስጠትም የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭን ለመተግበር በሂደት ላይ ይገኛል።
በመሆኑም ለዚህ ስራ ስኬታማነት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የሽግግር ፍትህን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ምክር ቤቱ እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የሽግግር ፍትህ ምንነት፣ አተገባበሩ፣ ከመደበኛ ህግ የተለየ መሆኑና አስፈላጊነት ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወነ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የምክክርና ውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ማህበረሰብን የማንቃት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ የማቋቋም ስራም ለአንድ ወገን የሚተው ባለመሆኑ የአለም አቀፍና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የማህበረሰብን አብሮነት የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ቀጣይነትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በፌደራል ደረጃ የተመዘገቡ ከ4 ሺህ በላይ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።