ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ምርቶችን ለገበያ ሊያቀርቡ የነበሩ  14 ተቋማት በሕግ እንዲጠየቁ ተደረገ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2015 (ኢዜአ)፦ በጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ምርቶችን ለገበያ ሊያቀርቡ የነበሩ 14 ተቋማት በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒትና  የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ገለጸ። 

የባለሥልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት በዳዳ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ24 ሺህ 804 የንግድ ተቋማት ላይ ቁጥጥርና ክትትል ተደርጓል።

ቁጥጥርና ክትትል ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የምግብ ማምረቻ፣ ማከፋፈያ፣ አገልግሎት መስጫና የችርቻሮ ንግድ ተቋማት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በ4 ሺህ 571 ተቋማት ላይ ከቃል ማስጠንቀቂያ ጀምሮ ተቋማቱን እስከ ማሸግ የሚደርስ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ነው የገለጹት።   

ይህም ብቻ ሳይሆን 14 ተቋማት በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉንና 100 ተቋማት ደግሞ ፈቃዳቸውን መልሰዋል ብለዋል።

እነዚህ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ያለማደስ፣ የጤና ምርመራ ካርድ ያለመኖር፣ ጊዜ ያለፈበትና የተበላሹ የምግብና የመጠጥ ምርቶችን ለገበያ ማዘጋጀት፣ ሕገ-ወጥ እርድና ምግብን ከበአድ ነገር ጋር በመቀላቀል ሕገ-ወጥ ድርጊት መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።

በጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ግምታቸው 19 ሚሊየን 647 ሺህ 962 ብር የሚጠጉ ምርቶች እንዲወገዱ መደረጉን ነው የገለጹት።

ከተወገዱ ምርቶች መካከል የምግብ፣ የተለያዩ ዓይነት የመጠጥ ምርቶችና የቤት ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

ሕብረተሰቡ ሕጋዊ ፈቃድ ከሌላቸው የንግድ ተቋማት ምንጫቸው የማይታወቁ ምርቶችን መግዛት እንደሌለበት መክረው፤ ከዋጋ ቅናሽ ይልቅ ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣይም ሕብረተሰቡ ለጤና ጉዳት የሚያደርሱ የተበላሹ  ምግብና መጠጥ ሲያጋጥመው 8864 ነፃ የስልክ መስመር እንዲያሳውቅ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብም እንዲሁ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ምርቶችን ከማቅረብ እንዲቆጠብም ነው ያሳሰቡት።

ባለሥልጣኑ ለተቋማት የድጋፍ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን በማከናወን ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲኖር የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም