ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት የህዝብን ሰላም ለማወክ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል--የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት የህዝብን ሰላም ለማወክ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል--የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን
አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2015 (ኢዜአ)፦ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት የህዝብን ሰላም ለማወክ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አሳሰበ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ለማስፋት የሚዲያ አዋጅ ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ ህጎች እንዲሻሻሉ አድርጓል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንዲስፋፉ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ነው ያሉት፡፡
በተለይም ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አዳዲስ መገናኛ ዘዴዎች ወደ ገበያው እንዲገቡ በማድረግ ዜጎች መረጃ በቀላሉ እንዲያገኙ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የበይነመረብ እና ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የስርጭት አድማስ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት የህዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላት ተበራክተዋል ብለዋል፡፡
የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎችን ለልማት፣ የተቸገሩ ዜጎችን ለመደገፍና ለአብሮነት የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ ከኢትዮጵያዊያን እሴት ውጪ ጥላቻን በማሰራጨት ላይ የተጠመዱ መኖራቸውን ነው የጠቆሙት፡፡
እነዚህ አካላት ዋነኛ ዓላማ የዜጎችን የአብሮነት እሴት በመናድ እኩይ ዓላማቸውን ማስፈጸም ስለመሆኑም ነው ያብራሩት፡፡
በመሆኑም ጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በግጭትና አለመረጋጋት የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል፡፡
የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃንን ከየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው መልዕክት መልቀቅ የሚያስችሉ በመሆናቸው መከታተል፣ መደገፍና መቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ አገርን የማስቀጠል መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መገናኛ ብዙኃን የአገርን ሉዓላዊ ጥቅም የሚጎዱ ሃሳቦችን ከማሰራጨት መታቀብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
መረጃ ተደራሽ የሚደርጉ አካላት አብሮነት የሚያጎሉ፣ ምርታማነት የሚያሳድጉ፣ የሰለጠነ የፖለቲካና የምርጫ ምህዳር እንዲኖር የሚያበረታቱ፣ ለአዲስ የትውልድ ቀረፃ ሚናቸውን የሚወጡ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡