ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን በተመለከተ የምታራምደውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በመጠቀም ይበልጥ ማስተዋወቅ ይገባል  

አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን በተመለከተ የምታራምደውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በመጠቀም ይበልጥ ለዓለም ማስገንዘብ እንደሚገባ አንድ ምሁር አመላከቱ።  

ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን ጥቅም ለማረጋገጥ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራንን ያካተተ ፎረም ተቋቁሟል።

የፎረሙ አባል የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ኢትዮጵያ አገሪቷ ከናይል ወንዝ የምታገኘው ጥቅም ላይ ምን ተግዳሮቶች አሉ? መፍትሔዎች ምን ምን ናቸው? በሚለው የጥናትና ምርምር ሥራዎች በማካሄድ ግብዓት የሚሆን ሃሳብ ያቀርባሉ።

አዲስ አበባና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አርባ ምንጭ እንዲሁም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረሙ በአባልነት አቅፏል።  

የፎረሙ አባል የሆኑት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍናና ሶሺዮሎጂ መምህር ዶክተር ተሾመ አበራ፤ "ሚዲያና ዲፕሎማሲ በናይል ወንዝ ላይ" በሚል ርዕስ የዳሰሳ ጥናት አካሂደዋል።

ዶክተር ተሾመ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን በተመለከተ የምታራምደውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በመጠቀም ይበልጥ ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኋን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ እየተወጡ ነው ወይ? ምሁራን ድርሻቸውን እያበረከቱ ነው ወይ? የሚለውን ማጤን እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።        

በተለይም ዲጂታል ሚዲያን በመጠቀም እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ውስንነት መኖሩን የተናገሩት ዶክተር ተሾመ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙኃን በተናበበ መልኩ መሥራት አለባቸው ብለዋል።       

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሕዝቡን ለማሰባሰብና ለማሳተፍ ትልቅ ሥራ ቢሰሩም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ግን አጀንዳ ቀርጸው የኢትዮጵያን እውነታ ማስተጋባት ላይ ግን ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በተለይም በአንጻራዊነት ብዙ ሕዝብ የሚናገራቸው በአረብኛና መሰል ቋንቋዎች አጀንዳዎችን ቀርጸው ተከታታይነት ያለው ሥራ ማከናወን ላይ ሊሰሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

አሁን ጊዜው የገጽ-ለገጽ ዲፕሎማሲ እየቀነሰ ያለበት ነው ያሉት ዶክተር ተሾመ ኢትዮጵያም ጊዜው የሚጠይቀውን የዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ ርብርብ ማድረግ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም ብለዋል።   

ቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያ ምን ያህል ኃብት አላት? እንዴት ወንዞቿን መጠቀም አለባት? እንዲሁም ትውልዱ በዚህ ረገድ ሉዓላዊነቱን እንዴት ማስከበር አለበት? በሚለው ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል።

ይህን ማድረግ ከተቻለ ለአገሩ ጠበቃ መቆም የሚችል እውቀት ያለው ዜጋ ማፍራት ያስችላል ሲሉም አንስተዋል። 

ትውልዱን የማስገንዘብ ሥራው በሥርዓተ-ትምህርት ሊታገዝ ይገባል ያሉት ምሁሩ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ትውልዱን በጥልቀት ማስገንዘብ ጠቃሚ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።      

 

     

 

                                   

 

           

 

             

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም