የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ ሩስሀይድሮ በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ ሩስሀይድሮ በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2015(ኢዜአ)፦ የሩሲያ የኢነርጂ ኩባንያ ሩስሀይድሮ(RusHydro) በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች ከሩስሀይድሮ የስራ ኃላፊዎች ጋር በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል የማምረት አቅም ቢኖርም የኢነርጂ አቅርቦቱ ከ50 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢነርጂ አቅርቦቱን ለማሳደግና በቀጣናው የተጀመረውን የኃይል ትስስር ለማስፋፋት ኢነርጂ የማምረት፣ የማሰራጨትና የማስተላለፍ አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ በበኩላቸው ከሕዝብ ቁጥር መጨመርና የኢነርጂ ፍላጎት እያደገ መሄድ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ኢነርጂ ማምረት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በኢነርጂ ልማት ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንና ለዚህ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሩስሀይድሮ የስራ ኃላፊዎች ለረጅም ጊዜ የቆየ የኃይል ማምረትና የማሰራጨት ልምድ እንዳላቸው ገልጸው በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በኃይል ልማት ዘርፍ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
እ.አ.አ 2004 የተቋቋመው ሩስሀይድሮ በሩሲያ ከሚገኙ ግዙፍ የኤሌትሪክ ኃይል ኩባንያዎች አንዱ ነው።