ቀጥታ፡

በአውሮፓ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/ 2015(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያደርጉትን ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ።

በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍቃዱ በየነ በጀርመን፣ ፖላንድና ቼክ ሪፐብሊክ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ፍቃዱ ኢትዮጵያ በለውጡ ሂደቶች ላይ ያሳካቻቸው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶች እንዲሁም የነበሩ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች፣ በሽግግር ፍትሕ ሂደት፣ በሕዳሴ ግድብ እና በ’ገበታ ለትውልድ’ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢና ስጦታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ‘ገበታ ለትውልድ’ ኢትዮጵያን የሚያኮራና ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ አገራዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ዳያስፖራው ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዳያስፖራው እውነታውን በመረዳት ለአገሩ ሁለንተናዊ ልማት ተሳትፎ ማድረግ አለበት ብለዋል።

ዳያስፖራው በኤምባሲው አገልግሎት አሰጣጥና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች አምባሳደሩ ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸውን በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም