ቀጥታ፡

 በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ተደራጅተው በመስራት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሀረና እና ደሎ መና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ

ጎባ ሚያዝያ 10/2015(ኢዜአ) በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ሥር ተደራጅተው በመስራት ተጠቃሚ መሆናቸውን በባሌ ዞን የሀረና እና ደሎ መና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

በሁለቱ የባሌ ዞኖች ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ በደን የተሸፈነ መሬት በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር እየለማ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ነው።

በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ማህበራቱ ስር ተደራጅተው የተፈጥሮ ደንን ከመንከባከብ በተጓዳኝ ከካርቦን ሽያጭ ከ179 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘታቸውም ተገልጿል፡፡

በሀረና ወረዳ ገርቢ ጋሎ ቀበሌ የዳዱሬ የደን ልማት ማህበር ኃላፊ አቶ አህመድ ከማል እንዳሉት፤ በደኑ ላይ ከመደራጀታቸው በፊት በአካባቢያቸው የሚገኘውን ሰፊ የደን ሀብት ለጊዜያዊ ጥቅም ሲባል ውድመትና ጭፍጨፋ ያደርሱበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግን ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ሆነው በአሳታፊ የደን ልማት ማህበር ስር በመደራጀት ደንን ከጭፍጨፋና ውድመት በመጠበቅ በውስጡ ንብን በማነብና በሌሎችም ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም በማህበራቸው ከ11 ሺህ ሄክታር ለሚሆን የተፈጥሮ ደን እንክብካቤ እያደረጉ  በሁለት ዙር ከተከናወነው የከርቦን ሽያጭ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ  ማግኘታቸውንም አመልክተዋል፡፡

የደሎ መና ወረዳ ጭሪ ቀበሌ የብርቢርሳ የደን ልማት ማህበር ተወካይ አርሶ አደር ጀማል ከድር በበኩላቸው ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ከ5ሺህ ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ደን በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የደን ኃብቱን በመንከባብ የአካባቢያቸውን የተፈጥሮ ሚዛን ከመጠበቃቸው በተጓዳኝ ከከርቦን ሽያጭ  በሁለት ዙር 9 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸውን ነው ያስረዱት፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት፣ በደን ሀብቱ ውስጥ ማርን ማምረት ከጀመሩ አምስት ዓመታት ወዲህ በሚያገኙት ተጨማሪ ገቢም ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። 

በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ታቅፈው ደኑን በመንከባከብ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ የእርሻ መሬት ለማስፋፋትና በህገወጥ አጠቃቀም በደኑ ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት መቀነስ መቻላቸውን የማህበራቱ ተወካዮች አስረድተዋል፡፡ 

በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አብደታ እንዳሉት፣ የተፈጥሮ ደንን ከውድመት ለመታደግና ህብረተሰቡም ከደኑ ተጠቃሚ እንዲሆን በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራበት ነው፡፡

በዚህም በሁለቱ የባሌ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ብቻ ከ16 ሺህ 800 የሚበልጡ አርሶ አደሮች በ38 ማህበራት ሥር ታቅፈው የደን ሀብቱን እንዲንከባከቡና ከልማቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሮቹ በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ታቅፈው ከ260 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ደን ላይ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ከ179 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ከከርቦን ሽያጭ ገቢ ማግኘታቸውን ነው የገለጹት፡፡

በውስጡም የንብ ማነብ ተግባራትና ያረጁ ዛፎችን ለማገዶና ሌሎች ተግባራት በማዋል ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውቀዋል። 

አርሶ አደሮቹ ደኑን በባለቤትነት መንካባከብ ከጀመሩ ወዲህ በፊት ከሰልና የጣውላ እንጨት ፍለጋ ሲጨፈጨፍ የነበረውን የደን ሀብት ማዳን መቻሉንም አስታውቀዋል። 

በባሌ ዞን ከ560 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው መሬት በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ መሆኑን ከኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የባሌ ቅርንጫፍ የተገኘው መረጃ ያመልክታል። 

በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ስር ከታቀፉት የተፈጥሮ ደኖች መካከል የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካል የሆነውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት በተጠባባቂነት የተመዘገበው “የሀረና ደን” እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሁለቱ የባሌ ዞኖች በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር ማህበራት ሥር የተደራጁ አርሶ አደሮች ባለፉት አምስት ዓመታት በተፈጥሮ ደኖች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭፍጨፋ በመቀነስ ባደረጉት እንክብካቤና ጥበቃ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የተቃጠለ አየር ወደ ህዋ እንዳይለቀቅ ማድረግ ችለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም