ቀጥታ፡

የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው--ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2015(ኢዜአ)፦የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

የጎረቤት አገር ሱዳን ህዝቦች ከጥንትም ጀምረው ነፃነታቸውን የሚወዱ እና ብሄራዊ ክብራቸውን አስጠብቀው የቆዩ ህዝቦች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የሱዳን ህዝብ ከሚወሳባቸው አያሌ መልካም ባህሪያት መሀከል ለጋስነት እና እንግዳ ተቀባይነታቸው ከምንም በላይ ጎልቶ ይጠቀሳል ብለዋል።

እነዚህ እሴቶች ደግሞ ከማህበራዊ ትስስሩ በላይ የኢትዮጵያን እና የሱዳንን ህዝብ የሚያመሳስሉ እና ይበልጥ የሚያቆራኙ ብለውም ከሌላው እንዲለዩ ከሚያረጓቸው እውነታዎች ሁነው እናገኛቸዋለን ሲሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም የሱዳን ህዝብ በባህሪው ኩሩ በመሆኑ በምንም ሁኔታ ክብሩን እና ነፃነቱን አሳልፎ የሚሰጥ አያደርገውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሆነም የሱዳን ህዝብ የራሱን ችግር በራሱ የመፍታት ታላቅ ዓቅም እና ጥበብ ያለው ታላቅ ህዝብ በመሆኑ ማንኛውም የሁከት ዓላማን ያነገበ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያስተናግድ አይሆንም” ብለዋል።

ስለዚህም እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህ ኩሩ የሱዳን ህዝብ አሁን ላይ እየገጠመው ያለውን ቀውስ በጥበብ ሊወጣው ይችላል ስንል ያለንን ፅኑ እምነት ለመግለፅ እንወዳለን ሲሉም አስረድተዋል።

የሱዳን ህዝብ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ መተው ያለበት ሲሆን የማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት ዓላማም ሰላምን እና ድርድርን በተመለከተ ብቻ ሊሆን ይገባል እንላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዛ ውጭ በሆነ በማንኛውም ድብቅ አጀንዳ የተነሳሳ የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴ በታሪክ ሸንጎ ላይ ተጠያቂ የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ በበኩሉ የሱዳን ህዝብ የውስጥ ችግሩን በለመደው ጥበባዊ አካሄድ በራሱ እንዲፈታ የሚመኝ እና የሱዳን ህዝብ ጥቅም ተከብሮ ማየት ትልቁ ፍላጎቱ መሆኑን በድጋሚ እየገለፅን አሁንም በህገወጥ መልኩ በአገሪቷ ውስጣዊ ችግሮች ወስጥ እጁን የሚሰድን ማንኛውም የውጭ ሀይልን በፅኑ እንቃወማለን ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም