የምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት በሙያና ክህሎት የሰለጠነ የሰው ሃብት ለማፍራት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት በሙያና ክህሎት የሰለጠነ የሰው ሃብት ለማፍራት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2015(ኢዜአ)፡-የምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት በሙያና ክህሎት ብቁ የሰው ሃብት ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የቀጣናው የዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
በፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ታንዛኒያ ያለውን አፈጻጸም የሚገመግም የሁለት ቀናት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በምስራቅ አፍሪካ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በማቀድ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
በእቅዱ መሰረትም በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ታንዛኒያ ላለፉት አራት ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የአገራቱን የሰው ሃብት አቅም ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትን ተመልክቷል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ፤ በፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በ150 ሚሊዮን ዶላር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በሚገኙ ሰባት ቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከላት እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመው በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ፣ በባቡር ትራንስፖርት፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በግብርና ማቀነባበርና መሰል ዘርፎች ተለይተው ላለፉት አራት ዓመታት ሲተገበር መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ከተመደበው እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ለግንባታ ወጪ መሸፈኑን ጠቁመው ለተግባር ተኮር ስልጠና የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ግዥ እንዲፈጽሙ በማድረግ አቅማቸውን የመገንባት ስራም ተከናውኗል ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሀፊ ፕሮፌሰር እድሪስ ራይ፤ በቀጣናው በሙያና ክህሎት ብቁ የሰው ሃብት ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት በትግበራ ለአገራት የተሞክሮ ልውውጥም ከፍተኛ ፋይዳ አለው ሲሉ ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ ተወካይ ዚዮሃን ሊያንግ፤ በበኩላቸው የዓለም ባንክ በአፍሪካ የሰው ኃይል ልማቱ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የ300 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለት እየተከናወነ ባለው ፕሮጀክት የዓለም ባንክና የምስራቅ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሚያስተባብሩት ሲሆን በቀጣናው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተደራሽነትን ማስፋትና ቀጣናዊ ትስስርን ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።