የጭነት ተሽከርካሪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል የተባለ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2015(ኢዜአ) ፡-የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ትሬድ ማርክ አፍሪካ የኢትዮጵያን የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎትን በማዘመን የወጪ እና ገቢ ንግድን ማሳለጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ እና በትሬድማርክ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታዬ ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት ትሬድማርክ አፍሪካ የጭነት ተሽከርካሪዎች የተቀናጀ፣ ቀልጣፋ እና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መተግበሪያ በማልማት አገልግሎት ላይ ያውላል ተብሏል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ስምምነቱ በሎጅስቲክስ ዘርፉ ያሉትን አሰራሮች የሚያዘምን ነው።

ምርትና አገልግሎቶች በተመጣጠነ ዋጋ እንዲቀርቡ ከማድረግ ባሻገር ከሌሎች አገራት ጋር ያለው የሎጅስቲክስ ስርዓት እንዲሳለጥ ያደርጋል ነው ያሉት።

ስምምነቱ የጭነት ተሽከርካሪዎች የተሳለጠ፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑም እንዲሁ።

በስምምነቱ መሰረት በፍጥነት ወደ ተግባር ለመሻገር የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በትሬድማርክ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታዬ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው በስምምነቱ መሰረት መተግበሪያውን በአንድ ዓመት ውስጥ አልምቶ ወደ አገልግሎት እንደሚያስገባ ጠቅሰዋል።

መተግበሪያው አገልግሎት ላይ ሲውል ኢትዮጵያ ያላትን የጭነት ተሽከርካሪ ሀብት መረጃ በአግባቡ በመመዝገብ በአንድ ማዕከል እንድትቆጣጠር እና በተቀጣለፈ ሁኔታ ምደባ በመስጠት በአግባቡ እንድትጠቀም ያስችላል ነው ያሉት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም