ቀጥታ፡

በመዲናዋ ከ15 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ የፊታችን ሀሙስ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2015(ኢዜአ)፡-ከ15 ሺህ በላይ የመዲናዋ ወጣቶች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ የፊታችን ሀሙስ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በሰጡት መግለጫ፤ የውይይቱ ዓላማ ወጣቶች ሀገራዊ ለውጡ ያስገኛቸውን ስኬቶች እንዲሁም ተግዳሮቶች በአግባቡ ተገንዝበው ለውጡን የበለጠ ውጤታማ  በማድረግ ሂደት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ነው ብለዋል።

ወጣቶች ለውጭ እና የውስጥ አፍራሽ ኃይሎች አጀንዳዎች ተጋላጭነታቸውን በመቀነስ የተሻለችና ለሁሉም የምትመች ሀገርን በመገንባት ረገድ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማስፈለጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ በላይ በከተማው ባሉ የብሎክ አደረጃጀቶች እና በሁሉም ወረዳዎች ከመጋቢት 28 እሰከ 30 ባሉት ቀናት ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ በነገው ዕለት በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ይቀጥላል ነው ያሉት።

እነዚህን ውይይቶች ተከትሎም ከሁሉም የመዲናዋ አካባቢዎች የተውጣጡ 15 ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉበት የማጠቃለያ ውይይት የፊታችን ሀሙስ ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በውይይቱ ሀገራዊ ለውጡ ባስገኛቸው ስኬቶች፣ ባጋጠሙ ፈተናዎች፣ እንዲሁም ባሉ መልካም ዕድሎች ዙሪያ  ለወጣቶች ማብራሪያ እንደሚሰጥ ገልጸው፤ በዚህም የጋራ መግባባት ይፈጠራል ነው ያሉት።

የመዲናዋ ወጣቶች የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ በመሆናቸው ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠልም የውይይቱ አንደኛው ዓላማ እንደሆነ ገልፀዋል።

የወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማስፋትም በከተማዋ ያሉ ሀብቶች እና ጸጋዎችን አሟጦ ስለመጠቀም  በዕለቱ ምክክር ይደረጋል ነው ያሉት።

በመድረኩ ከወጣቶቹ የሚነሱ ጥያቄዎች በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ እንደሚሰጥባቸው ነው አቶ በላይ የጠቆሙት።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሲቪክ ማህበራት፣ የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም