ሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ከ 232 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ከ 232 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሰራ ነው
ሀዋሳ ሚያዝያ 9/2015(ኢዜአ)---የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከ232 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ የዕድሳትና ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ሰርቢሶ ለኢዜአ እንዳሉት ከ20 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ምንም እድሳት ሳይደረግለት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ሆስፒታሉ ከሲዳማና ደቡብ ክልሎች በተጨማሪ ከኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችም ለሚመጡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመንና የተገልጋዩን ህዝብ ቅሬታ ለመፍታት ከ232 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጀቱ ከመንግስትና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች መገኘቱን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመው፣ እየተሰሩ ካሉ ተግባራት መካከል የአገልግሎት መስጫ ሕንጻዎች እድሳትና ዘመናዊ የሕክምና ምርመራ መሳሪያዎችን የማሟላት ሥራ በዋናነት እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል።
እስካሁንም አገልግሎት አሰጣጡን የሚያዘምኑ አዲስ ሲቲስካን፣ የኤምአርአይ፣¸የራጅና ሌሎች አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች ተሟልተው ወደሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ነርስ አገልግሎት ምክትል ሀላፊ ሲስተር ሀይማኖት ግዛቸው በበኩላቸው "ሆስፒታሉ ቀደም ሲል ካለው ውስን የምርመራ መሳሪያ አንጻር በርካታ ሕሙማን ለላቦራቶሪና ሌሎች ምርመራዎች ወደ ውጪ ይላኩ ነበር" ብለዋል።
በእዚህም ሕሙማን ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ለማስቀረትና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ሆስፒታሉ አስፈላጊ የምርመራ መሳሪያዎችን በሆስፒታሉ ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በእዚህም የተገልጋይን እንግልት ከማስቀረት ባለፈ ሆስፒታሉ ዘመናዊ ሕክምናዎችን ለመስጠት እያስቻለው መሆኑን አስረድተዋል።
ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጥ በተለይ ከቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ ከህዝቡ ቅሬታዎች ይነሱ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ የሆስፒታሉ ቺፍ ክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ክብሩ ክፍሌ ናቸው።
"የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማጠናከር በተደረገ እንቅስቃሴ ራሱን የቻለ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጫ በአዲስ መልክ ለማደራጀት ተችሏል" ብለዋል።
ሕጻናትና በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የአጥንት መሰበር ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለብቻ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ማዕከል መቋቋሙንም ገልጸዋል።
የሲቲስካን፣ ኤም.አር.አይ፣ ራጅና ሌሎች የምርመራ አገልግሎቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑንና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የህክምና መረጃ አያያዝ ሥራ ተግባራዊ ማድረግ እንደተቻለ ዶክተር ክብሩ ተናግረዋል።
ለአጥንት ህክምና ወደሆስፒታሉ የመጡት አቶ አሰፋ አዲሱ ቀደም ሲል የሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ተገልጋይን ያማርር እንደነበር አስታውሰው አሁን በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል እንዳሳየና በሀኪሞችም የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ400 በላይ ተኝቶ ታካሚዎችንና በቀን ከ10 እስከ 20 ሺህ ለሚሆኑ ተመላላሽ ሕሙማንም አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።